17/06/2026
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሰራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሄዱ
////////
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሰራተኞች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች፣ በተቋሙ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ አፈጻጸም እና በካፒታል ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂደዋል።
ውይይቱን የከፈቱት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር እና በዓለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ ክልል ፕሬዚዳንት ዶክተር ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፣ መድረኩ ኢትዮጵያ 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ካከናወነች በኋላ የተካሄደ በመሆኑ ለሀገራዊ ጉዳዮች የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
በዚሁ ወቅት ዶክተር ፈጠነ ተሾመ የኢንስቲትዩቱን የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ (2013–2022 ዓ.ም.) አፈጻጸም እና የካፒታል ፕሮጀክቶችን እንቅስቃሴ በተመለከተ ዝርዝር ገለጻ አቅርበዋል።
ተሳታፊዎችም በቀረበው ገለጻ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ተቋሙ በተለያዩ ዘርፎች ያስመዘገባቸውን ውጤቶች አድንቀው፣ ወደፊት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ የሚያስችሉ ገንቢ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ዶክተር ፈጠነ ተሾመ፣ በበጀት ዓመቱ የቀሩ ተግባራትን በፈጣንና ውጤታማ አሰራር በማጠናቀቅ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ አመራሩና ሰራተኞች በቅንጅትና በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
ውይይቱ በተቋሙ የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ በመፍጠር እና የተቋሙን የአፈጻጸም ውጤት የበለጠ ለማሻሻል የሚያግዙ ሀሳቦችን በማሰባሰብ ተጠናቋል።
13/06/2026
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር እና በአለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፈጠነ ተሾመ ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪ መመረቂያ ፅሁፋቸውን አቅርበው በእጅግ በጣም ጥሩ ውጤት በማምጣት አጠናቀዋል ። እንኳን ደስ ያሎት!!! እንኳን ደስ ያለን!!!!
12/06/2026
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት 100 ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ ጣቢያዎችን ለመግዛት ከጣሊያኑ የSIAP+MICROS S.P.A የውል ስምምነት አደረገ፡፡
//////
በውል ስምምነቱ ወቅት የኢንስቲትዩቱ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ(ዶ/ር) እንደገለጹት የሚገዙት ዘመናዊ የአየር ሁኔታ መመዝገቢያ ጣቢያዎች የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት በሚተገበርባቸው የአዋሽ፤ ስምጥ ሸለቆ እና ኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች ላይ የሚተከሉ መሆናቸውን ገለጻ አድርገዋል፡፡ በሌላ በኩል የSIAP+MICROS S.P.A ድርጅት የቢዝነስ ስራ አስፈጻሚ አቶ ማሪዮ ሞንታሪዮ እንደገለጹት ዘመናዊ ጣቢያዎቹን 4 ወራት ውስጥ ለማስረከብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
12/06/2026
እ.ኤ.አ ከጁን 11 እስከ 20/2026 (ሰኔ 4 እስከ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም) የሚኖረው የአየር ሁኔታ በውሃ ዘርፍ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ
///////
በሚቀጥሉት የጁን ሁለተኛዉ አስር ቀናት በክረምት ተጠቃሚ በሆኑ ተፋሰሶች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን የሚደረስ የገፀ ምድር የውሃ ፍሰት ይኖራቸዋል። በመሆኑም የሚኖረው የእርጥበት ሁኔታ ተፋሰሶቹ ከዕለት ወደ ዕለት የተሻለ የውሃ ይዘት እንዲኖራቸው አስዋጽኦ የሚያደረግ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ ቀናቶች የሚኖረው መልካም ዕድሎች በላቀ ሁኔታ ለመጠቀምና ተያያዥ ስጋቶችን ለመቀነሰ የሚከተሉትነ ተፋሰስ ተኮር የውሃ ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦችን ከወዲሁ መተግበር ያስፈልጋል
12/06/2026
እ.ኤ.አ ከጁን 11 እስከ 20/2026 (ሰኔ 4 እስከ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም) የሚኖረው የአየር ሁኔታ በግብርናው ሥራ እንቅስቃሴ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ
//////
በሚቀጥሉት የጁን ወር ሁለተኛው አስር ቀናት የመኸር እርሻ ስራ አስቀድመው በሚጀምሩ የበልግ ሰብል አብቃይ በሆኑ እንዲሁም በአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ከቀላል እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል። በመሆኑም የሚኖሩ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀምና የሚጠበቁ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ ከታች የቀረቡትን ቦታ ተኮር የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳብ ከወዲሁ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ፡፡
12/06/2026
እ.ኤ.አ ከጁን 11 እስከ 20/2026 (ሰኔ 4 እሰከ ሰኔ 13/2018 ዓ.ም) የሚኖረው የአየር ሁኔታ አዝማሚያ
///////////
በጁን የሁለተኛዉ አስር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በተለይም በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ ጥንካሬ እንደሚኖራቸው የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘም እርጥበታማው የአየር ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየተስፋፋ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸዉ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተጨማሪም በመካከለኛዉ፣ በምስራቅ እና በደቡብ የሀገራችን አካባቢዎች ቀላል መጠን ያለዉ ዝናብ ያገኛሉ፡፡
በሚቀጥሉት ቀናቶች ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች እና የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ መካከለኛ (ከ1-29 ሚ.ሜ) መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም አልፎ አልፎ በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ ምዕራብ እና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በ24 ሠዓት ውስጥ ከ30 ሚ.ሜ በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአጠቃላይ የሚኖረዉን የአየር ጠባይ ትንበያን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና የሚገኘውን የዝናብ መጠንና ስርጭት በአግባቡ በመጠቀምና በማሰባሰብ በዚህ ወቅት የሚካሄደውን የግብርና እንቅስቃሴ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር ማከናወን ያስፈልጋል፡፡
10/06/2026
ለኢንስቲትዩቱ ሰራተኞች በስነ ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥና የጥቅም ግጭት አስተዳደር ላይ ስልጠና ተሰጠ
//////////
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከፌዴራል የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር
በ“ስነ ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥና የጥቅም ግጭት አስተዳደር” ዙሪያ ለኢንስቲቲዩቱ አመራሮችና ሰራተኞች የአንድ ቀን ስልጠና ሰኔ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ተሰጠ ።
ስልጠናው ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በመጡ በዶ/ር ተስፋዬ ሂርጳሳ የተሰጠ ሲሆን በስነ ምግባራዊ ውሳኔ አሰጣጥ፣ በጥቅም ግጭት አስተዳደር እና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ገለጻ አድርገው ውይይት ተደርጎበታል ።
09/06/2026
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) የዓለም አቀፍ የአደጋ አስተዳደር ማህበር የምስራቅ አፍሪካ የፕሬዚዳንቱ የትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ አማካሪ ሆነው ተሰየሙ
/////////
የዓለም አቀፍ የአደጋ አስተዳደር ማህበር እንዳስታወቀው በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተበራከተ የመጣውን ከአየር ጠባይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አስጊ የአየር ሁኔታ ክስተቶችን ለመቀነስና ለመከላከል ከሀገራቱ የሚሰየሙ ባለሙያዎች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብሏል፡፡ በመሆኑም ዶ/ር አሳምነው ተሾመ የዓለም አቀፍ የአደጋ አስተዳደር ማህበር በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ ሀገሮች ማለትም ኢትዮጵያ፤ ኬንያ፤ ዩጋንዳ፤ታንዛኒያ፤ሩዋንዳ፤ቡሩንዲ፤ሶማሊያ፤ጂቡቲ፤ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን በየሀገሪቱ በሚሰጡ ትንበያዎችና ቅድመ-ማስጠንቀቂያዎች እንዲሻሻሉና አስጊ የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በአፍሪካ እና ከዚያ በላይ ያለውን ትብብር ለማስፋፋት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው ተቋሙ አስታውቋል።