12/06/2026
https://docs.google.com/forms/d/1UsOsegUMLmeoARy7bk9DZ1Z_eJLV15tYym-z1t9cx9c/edit
የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተገልጋዮች እርካታ ዳሰሳ ጥናት በኮሚሽኑ ተገልጋዮች እና ባለድርሻ አካላት የሚሞላ መጠይቅ
የታክስ ከፋዩን ማህበረሰብ ከግብር ሰብሳቢዉ ባለስልጣን በታክስ አከፋፈል የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመመርመር እና በማከራከር ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ ውሳኔ ይሰጣል
12/06/2026
https://docs.google.com/forms/d/1UsOsegUMLmeoARy7bk9DZ1Z_eJLV15tYym-z1t9cx9c/edit
የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የተገልጋዮች እርካታ ዳሰሳ ጥናት በኮሚሽኑ ተገልጋዮች እና ባለድርሻ አካላት የሚሞላ መጠይቅ
10/06/2026
የኮንትሮባንድ እቃ ጭኖ ሲጓጓዝ የተገኘ ተሽከርካሪ እስከ መውረስ የሚደርስ ቅጣት የሚያስቀጣው አዋጅ ጸደቀ፡፡
*******************
ፌታይኮ
የሕዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው በ24ኛ መደበኛ ስብሰባው የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን አጽድቋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮንትሮባንድ ንግድን በከፍተኛ ደረጃ ለመግታት የሚያስችልና የወንጀሉ ተባባሪ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን እስከ ሙሉ በሙሉ መወረስ የሚያደርስ ጠንካራ የቅጣት ድንጋጌ የያዘውን የጉምሩክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ በነበረው አዋጅ የኮንትሮባንድ ዕቃ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ባለቤቶች ይጣልባቸው የነበረው 100,000 የብር ቅጣት ዝቅተኛ በመሆኑ ወንጀሉን ከመቀነስ ይልቅ እንዲባባስ ማድረጉ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
አዲሱ ማሻሻያ እንደ ነገሩ ክብደትና እንደ ጭነቱ መጠን የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሠረት ተሽከርካሪን እስከመውረስ የሚያደርስ ቅጣት ይጥላል።
በተለይም ዕቃዎችን ለመደበቅ እንዲያስችል ተደርጎ የተሠራ፣ የተለወጠ ወይም ልዩ መደበቂያ አካል የተገጠመለት ተሽከርካሪ ከተገኘ፣ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭኖ ከተያዘ የማጓጓዣው ዕቃ ግምታዊ ዋጋ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ተሽከርካሪው ተወርሶ የመንግሥት ንብረት እንዲሆን አዋጁ ደንግጓል።
ይሁን እንጂ ማጓጓዣው ከመወረሱ በፊት የማጓጓዣው ባለቤት ይህንኑ እንዲያውቀውና ተሽከርካሪው ለኮንትሮባንድ ጥቅም ላይ ስለዋለበት ሁኔታ የመከላከያ ማስረጃ የመቅረብ ዕድል እንደሚሰጠውም ተመላክቷል።
አዲሱ አዋጅ ቀደም ሲል የዜጎችን አቤቱታ የማቅረብ መብት ይገድብ ነበር የተባለውን የአሠራር ሥርዓትም አሻሽሏል። ቀደም ሲል አንድ አስመጪ በጉምሩክ ኮሚሽን በተጠየቀው ቀረጥና ታክስ ላይ ቅሬታ ኖሮት ለታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አቤቱታ ማቅረብ የሚችለው የተጠየቀውን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ከከፈለ በኋላ ብቻ ነበር። በአዲሱ ማሻሻያ ግን አስመጪው ያመነበትን ቀረጥና ታክስ ከፍሎ፣ ልከፍል አይገባም የሚለውን አከራካሪ ቀረጥና ታክስ ሃምሳ በመቶ ብቻ በማስያዝ ይግባኝ ማቅረብ እንዲችል ተደርጓል።
ይህ አዲስ የተሻሻለው አዋጅ በሕገ-ወጥ የኮንትሮባንድ ንግድ ላይ የሚሳተፉ አካላትን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ደኅንነት ለመጠበቅ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን
ነፃና ገለልተኛነት ለፍትሐዊ የታክስ ሥርዓት !
ፌስ ቡክ፡- https://www.facebook.com/ftacofficial
ቴሌግራም፡- https://t.me/ftac_official
ትዊተር፡- https://twitter.com/federal_appeal
ዩ ቱብ፡- https://www.youtube.com/channel/UCzpuuuXybdHh7BlgWXMVIGw
08/06/2026
አለባበስ የሞያ ክብር መገለጫ አካል ነው!
********************
ፌታይኮ
የአለባበስ ኮድ/ደንብ (Dressing Code) የመተማመን ምልክት፣ የዲሲፕሊን ምልክት እና የሙያ ምልክት ሲሆን ዳኞች እና ጠበቆች የሚለብሱት ጋወን /ካባ ለፍርድ ቤት እና ለፍትህ ያለው ክብር እና ታማኝነት ማሳያ ነው፡፡
የተለያዩ ጽሁፎች እንደሚያመላክቱት ጥቁር ቀለም በብዙ የአለማችን ክፍል የህግ ሞያ የደንብ ልብስ በመሆን የሚያገለግል ሲሆን ጥንካሬን እና ስልጣንን የሚያመለክት ስለመሆኑ ይነገራል። ጥቁር ራስን መግዛትን ስለሚወክል የህግ ባለሞያዎች ዳኞችንም ጨምሮ ለፍትህ መገዛታቸውን ለማሳየት ጥቁር ይለብሳሉ።
ጥቁር ቀለም የክብር፣ የጥበብ እና የፍትህ ምልክት ስለሆነ ሁሉም የህግ ባለሞያዎች እና ዳኞች ሊከተሏቸው የሚገቡ እሴቶች እንደሆነ እና 'ጥቁር ልብስ' የስልጣንን፣ የእውቀትን፣ የጥንቃቄ እና የፅናት መልእክትን ያስተላልፋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ‘ጥቁር ካባ' መልበስ በህግ ባለሞያዎች መካከል የዲሲፕሊን ስሜት በመፍጠር የመብትና የፍትህ ተቆርቋሪ የመሆን ስሜትን ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል፡፡
የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ዳኛ ጥቁር ካባ መደብ ላይ ከአንገት እስከ እግር ጫፍ የሚደርስ ቢጫ ወርቃማ ቀለም ያለው ካባ እና ከአንገት የሚጀምር ሁለት ሰማያዊ መነሳንስ እንዲሁም በካባው ሁለቱ እጀታ ላይ ሶስት ቢጫ ወርቃማ መስመር ያለው ነው፡፡ ይህም ኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ እና ፍትሐዊ ውሳኔ እንደሚሰጥ ማሳያ ነው፡፡
በሀገር ልጅ የሚባክን ጊዜ የለም
26/05/2026
እንኳን ለኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1ሺህ 447ኛው ለኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም አደረሳችሁ።
በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የአብሮነትና የፍቅር እንዲሆንልዎ ልባዊ ምኞቱን የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ይገልጻል።
ኢድ ሙባረክ!
የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን
ነፃና ገለልተኛነት ለፍትሐዊ የታክስ ሥርዓት!
የኮሚሽኑን ውሳኔዎች ለማግኘት ይህን ይጫኑ 👉 https://t.me/ftac_official
የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን
ነፃና ገለልተኛነት ለፍትሐዊ የታክስ ሥርዓት !
20/05/2026
የትዕዛዝ፣ የብይን፣ የፍርድ እና ዉሳኔ የህግ ትርጉም
እነዚህ አራት ቃላት በሕግና በፍርድ ቤት የሥራ ሂደት ዉስጥ ተመሳሳይ ቢመስሉም የራሳቸው የሆነ የተለየ የሕግ ትርጉምና ደረጃ አላቸው፡፡
ትዕዛዝ
ትእዛዝ ማለት አንድ የፍርድ ቤት ክርክር ከመጀመሩ በፊት ወይም በሂደት ላይ እያለ ፍርድ ቤቱ አንድን ነገር እንዲደረግ ወይም እንዳይደረግ የሚሰጠው መመሪያ ነው።
ብይን
ብይን የሚሰጠው በክርክሩ ሂደት ዉስጥ ለሚነሱ መከራከሪያ ነጥቦች ምላሽ ለመስጠት ነው።
ፍርድ
ፍርድ ማለት ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን ማስረጃዎች መርምሮ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶና መዝኖ የሚሰጥ የመጨረሻ ድምዳሜ ነው።
ዉሳኔ
ዉሳኔ በፍርድ ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ ተግባራዊ ትዕዛዝ ነው።
ሚዲያ ዳሰሳ
የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት ከኢቲቪ ጋር ያረጉት ቆይታ
የሙክት በጎቹ እጣ ፈንታ
በይግባኝ ባይ አቶ ሁነኛው ፀጋዬ እና በጉምሩክ ኮሚሽን መካከል ሲደረግ የነበረው የሙክት በጎች የውርስ ክርክር ከፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እስከ ጠቅላይ ፍረድ ቤት ደርሷል፡፡ የበጎቹ እጣ ፈንታ ምን ይሆን? እነዚህ ሙክት በጎች ተገኝተው ለባለቤቱ አቶ ሁነኛው ተመለሱ? ወይስ ለዘላለሙ በጉምሩክ ኮሚሽን ተከረቸሙ?
መልካም ንባብ !
ይግባኝ ባይ አቶ ሁነኛው ፀጋዬ ብዛታቸው 97 የሆኑ ሙክት በጎች በብር 1‚505‚000 ከአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ በመግዛት በጎቹን ለፋሲካ በዓል የትግራይ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው መቀሌ ለመሸጥ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-22356 አ.አ በሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ በማጓጓዝ ላይ እንዳለ በአፋር ክልል ሚሌ ወረዳ የጉምሩክ ሚሌ መቆጣጠሪያ ኬላ ሰራተኞች መኪናውን በማስቆም ስለ በጎቹ መረጃ ሲጠይቁ ይ/ባይ በዘርፉ ያለውን የንግድ ፈቃድ እና የእንስሳቱን የጉዞ መሸኛ ቢያቀርብም የጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች ብዛታቸው 97 የሆኑትን በጎች ወደ ሚሌ የእንስሳት ማቆያ ጣቢያ፣ የንግድ ፈቃድ እና የጉዞ መሸኛ ለሰመራ ጉምሩክ ቅ/ፅ/ቤት በመላክ ቅ/ፅ/ቤቱ በቁጥር 73/5500/16 ሚያዚያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በጎቹን ውርስ ማድረጉን ለይግባኝ ባይ አሳውቋቸዋል፡፡
ይግባኝ ባይ አቶ ሁነኛው በክርክራቸው መ/ሰጪ ጉምሩክ ለውርሱ መሠረት ያደረገው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በቁጥር 01.85/46024 ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም ለአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ንግድ ቢሮ የፃፈውን ደብዳቤ እና የቁም እንስሳት ግብይት አዋጅ ቁጥር 819/2006 አንቀፅ 17ን በማጣቀስ ሲሆን ነገር ግን የአዋጁ አንቀፅ 17 ድንጋጌ እና የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፃፈው ደብዳቤም ቢሆን ጉምሩክ ኮሚሽን በጎቹ ላይ የውርስ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ በህግ የተሰጠው ስልጣን እንደሌለው ለችሎቱ ገልጿል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የፃፈው ደብዳቤ መዳረሻቸውን ሰመራ፣ በባቢሌ ወደ ሱማሌ ክልል ፋፈም ዞን አካባቢዎች እና ወደ ሀገሪቱ የመውጫ መስመሮች ላይ ወደሚገኙ ቦታዎች ለሚያደርጉ ሀገር ውስጥ የቁም እንስሳት ግብይት ተዋናዮች የተለየ መመሪያ እስካልተሰጠ ድረስ የማጓጓዣ ፈቃድ እንዳይሰጥ ለአፋር ክልል ንግድ ቢሮ የፃፈው ደብዳቤ ነው እንጂ የቁም እንስሳቱን ውርስ እንዲያደርጉ የሚል እንዳልሆነ እና የይ/ባይ በጎች መነሻቸው ደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ሲሆን መዳረሻቸው ደግሞ መቀሌ ከተማ በመሆኑ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በፃፈው ደብዳቤ መሠረት መነሻቸውና መዳረሻቸው በደብዳቤው ላይ ከተገለፁት ከተሞች ውስጥ በሌለበት መ/ሰጪ በበጎቹ ላይ ያስተላለፈው የውርስ ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑንም ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
በተጨማሪም በአማራ ክልል በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች በተለይም ራያ ቆቦ እና አላማጣ ወረዳዎች በጦርነት ምክንያት ከደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ ከተሞችን አቆራርጦ መቀሌ ከተማ የሚያስኬደው የአስፓልት መንገድ አስተማማኝ ሰላም የሌለበት መሆኑ እየታወቀ የጉዞ መስመራቸውን በመቀየር ሲጓጓዝ ተገኝቷል በሚል እና በጉምሩክ አዋጅ አንቀፅ 2(44) ለጉምሩክ የጠረፍ መስመር በሰጠው ትርጉም መሠረት ከኢትዮጵያ የጉምሩክ መስመር ወደ ውስጥ እስከ 15 ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ የሚገኝ ሥፍራ እንደሆነ የሚደነግግ ሲሆን የይ/ባይ በጎች የተያዙበት የሚሌ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ የሚገኝበት ሥፍራ በጉምሩክ የጠረፍ መስመር ውስጥ የሚገኝ ባለመሆኑና ይ/ባይ ሌላ የፈፀምኩት የህግ ጥሰት በሌለበት መ/ሰጪ ያስተላለፈው የውርስ ውሳኔ ተገቢ አይደለም ሊሻር ይገባል በማለት ተከራክሯል፡፡
መልስ ሰጪ ጉምሩክ ኮሚሽን በበኩሉ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባስተላለፈው ሰርኩላር ላይ ወደተጠቀሱት አካባቢዎች እና ወደ ሀገሪቱ የመውጫ መስመሮች ላይ ወደሚገኙ ቦታዎች (አፋር ክልል) በማድረግ ለሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ የቁም እንስሳት ግብይት ተዋናዮች የተለየ መመሪያ እስካልተሰጠ ድረስ ክልሎች እና የከተማ መስተዳደሮች ምንም ዓይነት የቁም እንስሳት የማጓጓዣ ፈቃድ መስጠት የማይችሉ ሲሆን ነገር ግን ይ/ባይ ያቀረቡት የጉዞ መሸኛ ወረቀት ላይ መድረሻቸው መቀሌ ተብሎ የተፃፈ ሲሆን በጎቹን ከአማራ ክልል ቀጥታ ወደ መቀሌ ማጓጓዝ የሚችልበት አጭር መንገድ እያለ ጉዞ መስመራቸውን በመቀየር የጉዞ መሸኛቸውንና የንግድ ፍቃድ እንደሽፋን በመጠቀም በጎቹን ወደ ምስራቁ የሀገሪቱ መውጫ በር ሚሌ ከተማ ጭኖ ሲንቀሳቀስ ተይዞ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በቁጥር 01.85/46024/15 ሚያዚያ 03 ቀን 2006 ዓ.ም በፃፈው ደብዳቤ የቁም እንስሳት ግብይት አዋጅ ቁጥር 819/06 እና የጥሬ ቆዳ እና ሌጦ ግብይት አዋጅ ቁጥር 814/06 ድንጋጌዎች መሠረት ቁጥጥር እንድናደርግ እና እንድናስፈፅም በሰጠን ውክልና መሰረት በበጎቹ ላይ የውርስ ውሳኔ መተላለፉ አግባብ ነው በማለት ለችሎቱ ያስረዳ ሲሆን ይ/ባይ ያቀረበው የጉዞ መሸኛ ወረቀት ስልጣኑ በህግ በታገደ አካል የተሰጠው በመሆኑ የበጎቹን ህጋዊነት የማያረጋግጥና መመሪያውን ለማስፈፀም በወጣው ደንብ ቁጥር 341/07 አንቀፅ 10(3) እና (15) መሠረት የክልል እና የከተማ መስተዳደሮች ቁም እንስሳት የጉዞ መሸኛ መስጠት የሚችሉት ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት እንደሆነ በግልፅ የሚደነግግ ሲሆን ይ/ባይ የደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መመሪያን በመተላለፍ የሰጠውን የጉዞ መሸኛ ያቀረበ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው እና ይ/ባይ መመሪያው ክልከላ የሚያደርገው መነሻቸውን ዳንሻ፣ መተማ፣ ቦረና፣ ባቢሌ፣ አዳማ እና መተሐራ የሚያደርጉ የቁም እንስሳት በአፋር ክልል አዋሽ ሰባትና ጭፍራ በማድረግ ወደ ሰመራ፣ ባቢሌ እና ወደ ፋፈም ዞን በማድረግ ወደ ጅቡቲ እና ሶማሌ ላንድ ለሚወጡ የቁም እንስሳትን እንጂ የይ/ባይ በጎች መነሻቸው አማራ ክልል ሆኖ መዳረሻቸው ደግሞ መቀሌ በመሆኑ መመሪያው ክልከላ አያደርግብኝም ያሉ ሲሆን አገሪቱ የተፈቀዱም ሆነ ያተፈቀደ አምስት መውጫ በሮች ያሏት በመሆኑ ክልከላው በሰርኩላሩ ላይ የተጠቀሱት አካባቢዎች ላይ ብቻ እንዳልሆነ ከደብዳቤው ይዘት መረዳት ይቻላል ሲል ለችሎቱ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን የግራ ቀኙን የፅሁፍና የቃል ክርክር አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎችና ከቀረቡት ማስረጃዎች ጋር በማገናዘብ “አከራካሪ በሆኑት ሙክት በጎች ላይ በመ/ሰጪ በኩል የውርስ ውሳኔ መተላለፉ አግባብ ነው? ወይስ አይደለም?” የሚለውን ጭብጥ በመለየት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
የጉምሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 እንዲሁም በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1160/2011 ኮንትሮባንድ እቃዎች እንዲወረሱ በግልጽ ሲደነግግ በአስፈጻሚው አካል በኩል ዕቃዎች በህጋዊ ሁኔታ የሚስተናገዱበት ስነ ስርዓት እንዲዘረጋ ኃላፊነት በመስጠት ነው፡፡ የጉምሩክ የማሻሻያ አዋጁ አንቀፅ 2(34)(1)(ሀ) መሰረት በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ወይም ወደ ውጪ የሚላኩ ዕቃዎች ውርስ ሆነው ለመንግስት ገቢ እንደሚደረጉ ይደነግጋል፡፡
በቀረበው ይግባኝ ላይ ጉምሩክ ሙክት በጎቹን ለመውረስ መነሻ ያደረገው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በቀን 24/09/2015 በቁጥር 01.85/46024/15 የጻፈዉን ደብዳቤ መሰረት በማድረግ መሆኑን ገልጿል፡፡ ከዚህ አንፃር በጉምሩክ የውርስ ውሳኔ የተላለፈበትን አግባብ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ሲመረምር የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከላይ በተገለፀው ቀንና ቁጥር ያስተላለፈው ሰርኩላር መዳረሻቸውን ወደ ሀገሪቱ መውጫ መስመሮች በማድረግ ለሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ የቁም እንስሳት ተዋናዮች የተለየ መመሪያ ካልተሰጠ በቀር ምንም አይነት የቁም እንስሳት የማጓጓዣ ፈቃድ መስጠት የተከለከለ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን ይህንን መመሪያ ተከትለዉ መስራት የሚገባቸዉ መመሪያው የተላለፈላቸው ወረዳዎች እና የከተማ መስተዳደሮች ሲሆኑ ይህን በመተላለፍ የይለፍ ወረቀት መስጠታቸው የአቶ ሁነኛውን ሙክት በጎች ህገ ወጥ የሚያስብል ካለመሆኑም በላይ መመሪያውን ተላልፎ የይለፍ ወረቀት የተሰጣቸዉ በመሆኑ ጉምሩክ ይህንን ደብዳቤ መነሻ በማድረግ ያቀረበውን ክርክር የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አልተቀበለውም፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን የተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት በቁም እንስሳት ግብይት አዋጅ ቁጥር 819/2006 ለንግድ ሚኒስቴር የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ የሚቻል ሲሆን ከዚህ አንፃር በቁም እንስሳት ግብይት አዋጁ የተቀመጡትን የንግድ ሚኒስቴር ስልጣንና ኃላፊነት በተመለከተ በአዋጁ አንቀፅ 15(1-10) በዝርዝር ከተቀመጠው አንዱ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዙ ወይም ግብይት ሲፈፀምባቸው የተገኙ የቁም እንስሳትን የመያዝ፣ የቁም እንስሳቱን እንደአግባቡ በመጀመሪያ ወይም በሁለተኛ ደረጃ የቁም እንስሳት ግብይት ማዕከል አቅርቦ በጨረታ በመሸጥ ገንዘቡን በዝግ የባንክ ሂሳብ እንዲቀመጥ የማድረግ፣ በዚህ አዋጅ አንቀፅ 17 መሰረት እንዲወረስ ሲወሰንም ለመንግስት ገቢ እንዲሆን የማድረግ ስልጣን ያለው መሆኑን ያስቀመጠ ሲሆን በአዋጁ አንቀፅ 17 የቅጣት ድንጋጌ ላይ ከቁም እንስሳት የግብይት ማዕከላት ውጪ የቁም እንስሳትን የሸጠ ወይም ለሽያጭ ያቀረበ ወይም የገዛ ማንኛውም ሰው የቁም እንስሳቱ እንደሚወረሱ እና ቀላል የእስራት ፍርድ እንደሚተላለፍ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በዚህ ድንጋጌ አግባብም ህገ-ወጥ የቁም እንስሳት ዝውውርን በተመለከተ የንግድ ሚኒስቴር ኃላፊነት በፍ/ቤት የሚሰጠውን የውርስ ውሳኔ መሰረት በማድረግ እንስሳቱን ሸጦ ለመንግስት ገቢ የማድረግ እንጂ አስተዳደራዊ የውርስ ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የሌለው መሆኑን ያሳያል፡፡
የመ/ሰጪ ባለሙያ ሎጊያ የድንበር መውጫ መሆኑን እንዲሁም ሎጊያ ከጉምሩክ ጠረፍ መስመር በአሳይታ በኩል 100 ኪ.ሜ እና በጋላፊ በኩል 200 ኪ.ሜ እንደሚርቅ ከሰጡት የምስክርነት ቃል ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ይህም በጎቹ ከጉምሩክ የጠረፍ መስመር በ15 ኪሎ ሜትር እርቀት ውስጥ አለመሆኑን ለመገንዘብ የተቻለ በመሆኑ ይ/ባይ ከዚህ አንፃር ያነሳውን መከራከሪያ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ተቀብሎታል፡፡
በመሆኑም መ/ሰጭም የሚያስፈፅመው የንግድ ሚኒስቴር በአዋጁ የተሰጠውን ኃላፊነት ብቻ ሆኖ እያለ ሙክት በጎች ከተያዙ በኋላ ተገቢውን ሂደት በመፈፀም በፍ/ቤት ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረግ ሲገባ ፍ/ቤት የውርስ ውሳኔ ባልሰጠበት ሁኔታ መ/ሰጭ የቁም እንስሳት አዋጅ ቁጥር 819/2016 አንቀፅ 17ን መሰረት በማድረግ ያስተላለፈው የሙክት በጎች የውርስ ውሳኔ የሕግ መሠረት እንደሌለው የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በውሳኔው አስፍሯል፡፡
በሌላ በኩል ይ/ባይ አቶ ሁነኛው ሙክት በጎች በጉምሩክ የተሸጡ መሆናቸውን በመግለፅ የበጎቹን ዋጋ እንዲመለስላቸው በመልስ መልሳቸው ላይ የጠየቁ ሲሆን ጉምሩክ ኮሚሽን በበኩሉ ሙክት በጎቹ የተገዙበት ዋጋ ተጋኖ የቀረበ መሆኑ እና ልንጠየቅ የሚገባው በሸጥንበት ልክ ነው ሲል በቃል ክርክር ወቅት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽንም ጉዳዩን ሲመረምር መ/ሰጪ ጉምሩክ በጎቹ በሞዴል ገቢ ሲደረጉ የተገመቱበትን ዋጋ የሚያሳይ ደረሰኝ ያቀረበ በመሆኑ በአንፃሩ በይ/ባይ በኩል የበጎቹን ትክክለኛ ዋጋ የሚያስረዳ ማስረጃ ስላልቀረበ በጎቹ በሞዴል ገቢ በተደረጉበት ዋጋ መሰረት ለይ/ባይ ተመላሽ ሊደረግለት ይገባል በማለት የመ/ሰጪን ውሳኔ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ሽሮታል፡፡
በፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ውሳኔ ቅር የተሰኙት መልስ ሰጭ የነበረው ጉምሩክ ኮሚሽን በተራው ይግባኝ ባይ በመሆን በመዝገብ ቁጥር 333504 ቅሬታቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡ ቢሆንም ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ ውሳኔ ምንም ጉድለት አላገኘሁበትም በማለት የጉምሩክ ኮሚሽንን አቤቱታ በብይን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
ጉምሩክ ኮሚሽን ይግባኝ ባይነቱን ቀጥሎበት በመዝገብ ቁጥር 276174 ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በስር ፍርድ ቤቶች የተሰጠው ውሳኔ የህግ ስህተት ስለተፈፀመበት ይታረምልኝ በማለት ይግባኝ አቤቱታ አቅርቧል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀረበው ቅሬታ ያስቀርባል በማለት ከተያዘው ጭብጥ እና አግባብነት ካላቸው የህግ ድንጋጌዎች በማገናዘብ መዝገቡን መርምሮታል፡፡ እንደመረመረውም ለዚህ ይግባኝ መሠረት የሆነው ንብረትነታቸው የአሁን መልስ ሰጭ የአቶ ሁነኛው ፀጋዬ የሆኑት 97 ሙክት በጎች በአሁን ይግባኝ ባይ እንዲወረሱ መደረጉ ያላግባብ ነው በሚል ይግባኝ ቅሬታ በመቅረቡ ሲሆን የአሁን ይግባኝ ባይ በበኩሉ የአሁን መልስ ሰጪ አቶ ሁነኛው በአዋጅ ቁጥር 819/2006 እና በንግድ ቀጠናዊ ሚኒስቴር በቀን 24/09/2015 ዓ.ም በቁጥር 01.85/46024/14 የተላለፈ ሰርኩላር በመተላለፍ ብዛታቸው 97 የሆኑ በጎች በአይሱዙ ተሽከርካሪ የጉዞ የይለፍ ወረቀት መሸኛ እንደ ሽፋን በመጠቀም የቁም እንስሳዎችን ጭነው ሲንቀሳቀሱ በሚሌ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉ ስለሆነ ውርስ መደረጉ አግባብ ነው በማለት ተከራክሯል፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የአሁን ይግባኝ ባይ ለክርክር ምክንያት የሆኑት በጎች ውርስ ማድረጉ በሌለው ስልጣን ነው በማለት የስር ፍርድ ቤቶች የደረሱበት ድምዳሜ በአግባቡ መሆን አለመሆኑን ጭብጥ በመያዝ ጉዳዩን እንደሚከተለው መርምሮታል፡፡
አቶ ሁነኛው በጎቹን ያጓጓዙት ከሚመለከታቸው አካላት የይለፍ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ስለመሆኑ በስር ኮሚሽኑ የተረጋገጠ ጉዳይ ሲሆን የጉምሩክ ኮሚሽን ክርክር የንግድ ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያስተላለፈው ሰርኩላር የቁም እንስሳት የማጓጓዝ ፍቃድ መስጠት ተከልክሏል በሚል ቢሆንም የይለፍ ወረቀቱ አቶ ሁነኛው ተሰጥቷቸው ይዘው የቁም እንስሳቶቹን ሲያጓጉዙ የተገኙ ሲሆን ይህ በሚሆንበት ጊዜ በሰርኩላሩ የእንስሳቶቹ መወረስ የሚያስከትል ስለመሆኑ የተመለከተ የለም፡፡ ለክርክር መነሻ የሆኑት በጎች የተያዙት የሚሌ ጉምሩክ ቅርንፃፍ ባለሙያ ሎግያ የድንበር መውጫ መሆኑን እና ከጉምሩክ ጠረፍ መስመር በአይሳኢታ በኩል 100 ኪ.ሜ እና በጋላፊ በኩል 200 ኪ.ሜ እንደሚርቅ በስር ኮሚሽኑ በሰጡት የምስክርነት ቃል የተረጋገጠ በመሆኑ ይህንንም በጎቹ ከጉምሩክ የጠረፍ መስመር በ15 ኪ.ሜ እርቀት ውስጥ የተያዙ ስለመሆኑ የማያሳይ እንደሆነ መገንዘብ የሚቻል በመሆኑ ከዚህ አንፃር የጉምሩክ ኮሚሽን ያቀረቡት ክርክር ተቀባይነት ያለው አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ጉምሩክ ለውርሱ እንደምክንያት በማድረግ የጠቀሱት የንግድ ሚኒስቴር በቀን 03/08/2006 በተሰጠ ውክልና በቁም እንስሳት ግብይት አዋጅ ቁጥር 819/2006 መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ይህ ማለት ህገ ወጥ የቁም እንስሳት ዝውውርን አስመልክቶ የንግድ ሚኒስቴር ስልጣን የሚሆነው በፍርድ ቤት ክስ ቀርቦ በሚሰጥ የውርስ ውሳኔ መሰረት እንስሳቱን በመሸጥ ለመንግስት ገቢ የማድረግ እንጂ አስተዳደራዊ የውርስ ውሳኔ የመስጠት ኃላፊነት የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ አግባብም የጉምሩክ ኃላፊነት በጎቹ ከተያዙ በኃላ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ ፍርድ ቤት የውርስ ውሳኔ ባልሰጠበት የቁም እንስሳዎቹ ውርስ ማድረጋቸው ከተሰጠው ስልጣን ውጪ ነው፡፡
አጠቃላይ ክርክሩ ከላይ በተመለከቱት ምክንያቶች የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ተገቢ ከሚባል የሚነቀፍ ሆኖ ስላልተገኘ በአብላጫ ድምፅ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመ/ቁ 333504 በቀን 25/04/2017 ዓ.ም ብይን እና የፌደራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን በመ/ቁ B-3064/17 በቀን 18/02/2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት የሰጡት ውሳኔ ለአቶ ሁነኛው ፀጋዬ ሙክት በጎቹ በአካል ባይመለሱላቸውም በጊዜው በጎቹን በሞዴል ገቢ በተደረጉበት ዋጋ መሰረት ተመላሽ ሊደረግ ይገባል በማለት የተሰጠውን ውሳኔ በፍ/ስ/ስ/ሕ/ቁ 348(1) መሰረት በማፅናት የማሀል ዳኛው በዚህ ክርክር የወጣውን ወጪ እና ኪሳራ በግራ ቀኙ የየራሳቸውን ይቻቻሉ በማለት መዶሻን ከጠረቬዛ ጋር በማዋሀድ መዝገቡን ወደ መዝገብ ቤት አስመልሰዋል፡፡