05/06/2026
“የማር ምርታማነትን ለማሳደግ የንብ ማነብ ሥራን ማዘመንና የከተማ ግብርናን ማጠናከር ወሳኝ ነው”
ፓዌ - ግንቦት 28/2018 ዓ.ም
የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል የማር ምርታማነትን ለማሳደግ የንብ ማነብ ሥራን ማዘመን፣ እንዲሁም የከተማ ግብርናን አካቶ በዘርፉ መሥራት ወሳኝ መፍትሔ መሆኑን አስታወቀ።
ምርምር ማዕከሉ በመተከል ዞን ፓዌ ከተማ 02 ቀበሌ ለሚገኙ አዲስ የተደራጁ አርሶ አደሮች እና የግብርና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ሰጥቷል። ሥልጠናው የንብ ማነብ ዕውቀትና ክህሎትን በማሳደግ፣ ባህላዊ አሠራርን ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመቀየር እና የከተማ ግብርናን ለማጎልበት ያለመ ነው።
የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ደስታ አበበ እንደገለጹት፣ ንብ ማነብ ለዜጎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር ለምግብ ዋስትና፣ ለሰብል ምርታማነት መጨመር እና ለአየር ንብረት ጥበቃ ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል። በተለይም የከተማ ግብርናን በንብ ማነብ ስራ በማቀናጀት፣ የከተማ ነዋሪዎች ባላቸው ውስን ቦታ ሳይቀር ምርታማ መሆን እንደሚችሉና ለምግብ ዋስትናው ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ ሀብቴ አረጋ በበኩላቸው፣ ማዕከሉ ያለውን ክፍተት በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ የተሻሻሉ ዘመናዊ የቀርከሃ ቀፎዎች እና የንብ ቀሰም እፅዋት ቴክኖሎጂዎችን ምርምር ማዕከሉ በማስተዋወቅ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም አስረድቶል።
እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በገጠር ብቻ ሳይሆን በከተማ ግብርና መዋቅር ውስጥም በቀላሉ ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው ብለዋል።
የፓዌ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አይቸው ሞገስ እንደገለጹት፣ አርሶ አደሮች እና የከተማ ግብርና ተሳታፊዎች የቴክኖሎጂ ድጋፉን ተቀብለው ወደ ተግባር እንዲገቡ ከቀበሌ እስከ ወረዳ ባሉ የግብርና ባለሙያዎች በኩል አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በመጨረሻም ምርምር ማዕከሉ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት፣ ከንብ አናቢዎች፣ ማኅበራት፣ ተቋማት እና የከተማ ግብርና ተሳታፊዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ አረጋግጧል።
29/05/2026
በፓዌ የግብርና ምርምር ማዕከል አርሶ አደሮችን ታሳቢ ያደረገ የካሼውነት ፍራፍሬና የሞቃታማ አካባቢ ቡና ዝርያዎች አመራረት ስልቶች ላይ ያተኮረ ተግባራዊ ስልጠና ተሰጥቷል።
በሆርቲካልቸር ምርምር ፕሮግራም አማካኝነት በካሼዉነት እና በሞቃታማ አካባቢዎች ለሚበቅሉ የቡና ዝርያዎች ሲከናወን የቆየው የምርምር እና የማላመድ ስራ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡን የፓዌ የግብርና ምርምር ማዕከል ገለጸ።
በዚህም መሰረት፣ ለተለያዩ የአየር ንብረት ሁኔታዎች ተስማሚ ሆነው የተገኙት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ለግብርና ማህበረሰቡ የማስተዋወቅ ስራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።
የሆርቲካልቸር ምርምር ፕሮግራም በከፍተኛ ጥንቃቄ የካሼዉነት እና በሞቃታማ አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑ የቡና ዝርያዎችን ለመለየትና ለማላመድ ጥልቅ ጥናቶችን ሲያካሂድ ቆይቷል።
የአካባቢውን የስነ-ምህዳር ሁኔታ መሰረት በማድረግ ምርታማነታቸው የላቀ፣ በሽታን የመከላከል አቅማቸው ከፍተኛ እና ለገበያ ተፈላጊነት ያላቸውን ዝርያዎች በማግኘት በአሁኑ ወቅት በምርምር የተገኙት እነዚህ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ እና በስፋት እንዲተገበሩ የማስተዋወቅና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው የመስክ ምርምር አሁን ላይ ወደ ተግባራዊ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። አርሶ አደሮቻችን እነዚህን ምርጥ ዝርያዎች በመጠቀም ምርታቸውን በጥራትና በብዛት እንዲያሳድጉና የኑሮ ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠርን ነው" ሲሉ ስልጠና የሰጡት የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
በቡና እና ሌሎች አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የጋራ ውይይቶችና የመስክ ጉብኝቶች ተደርገዋል።
ምርምር ማዕከሉ አርሶ አደሩ ዘመናዊ የቡና አዝመራ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም በማበረታታት፣ የቡና ምርትን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማሳደግና የኢትዮጵያን የቡና የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ላይ ይገኛል።
30/04/2026
የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት
በፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ለ6 ዓመት ተመራማሪነት እና የስራ ሂደት ተጠሪ ሆነው ያገለገሉ፣ ለ4 ዓመታት ደግሞ የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ሆነው ካገለገሉ በኋላ አዲስ ወደ ተከፈተው የወረኢሉ ግብርና ምርምር ማዕከል በመዛወር ከማቋቋም ባሻገር እስከ ተሾሙበት ቀን ድረስ ለ3 ዓመታት ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል። በቆዩባቸው ጊዜያትም ተቋሙን ውጤታማ ያደረጉ ስራዎችን አከናውነዋል።
ለሀገርና ለወገን የሚተርፍ ዕውቀትና የሥራ ትጋት የታጠቁት የቀድሞ ሥራ ባልደረባችን አቶ ደሳለኝ ተሻለ፤ ላለፉት 13 ዓመታት በግብርናው የምርምር ዘርፍ ያሳዩት ቁርጠኝነት ዛሬ ለታላቅ አገራዊ ኃላፊነት አብቅቷቸዋል።
እነዚህን ተከታታይ ውጤታማ የሥራ ጉዞዎችን ተከትሎ፣ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ አማካኝነት በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ሆነው ተሹመዋል።
ከመሠረቱ ተነስተው ዕውቀትንና ልምድን አከማችተው፣ ዛሬ ለዚህ ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት በመብቃትዎ ታላቅ ኩራት ይሰማናል።
ይህ ሹመት የልፋትዎ ውጤት፣ የትጋትዎ ምንዳ ነው። በአዲሱ የሥራ መስክዎ የኢትዮጵያን ግብርና ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግሩ ሙሉ እምነታችን ነው።"
ለዚህ ስኬትም የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል በመሉ የማዕከሉ ሠራተኞች ስም የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፏል።
08/04/2026
(ፓዌ:-መጋቢት 29/2018 ዓ.ም) በፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ለጥበቃ ሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት (EIAR) ስር በሚገኘው በፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል፣ የመሠረታዊ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ ስር ለሚገኙ የጥበቃ ሠራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል።
ሥልጠናውን የሰጡት የመሠረታዊ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ መርከቡ ደግዋለ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የጥበቃ ሠራተኞችን የሥራ አፈጻጸም እና ግንዛቤ ማሳደግ ነው።
ይህ ሥልጠና የማዕከሉን ደኅንነት እና የጥበቃ ሥራዎችን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አሰረድተዋል። ተሳታፊዎቹም በሥራቸው ላይ ሊያጋጥሟቸው ስለሚችሉ ጉዳዮች እና ስለሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ሰፊ ግንዛቤ አግኝተዋል።
በመጨረሻም፣ እንዲህ ያሉ አጫጭር ሥልጠናዎች የሠራተኞችን አቅም በመገንባት ረገድ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የማዕከሉ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።
04/04/2026
የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ለምርምር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ::
ፓዌ፣ ኢትዮጵያ – የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል (Pawe Agricultural Research Center) ከመጋቢት 24 እስከ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ሲሳጥ የነበረዉን የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናውን አጠናቋል።
ስልጠናው በማዕከሉ ውስጥ ለሚገኙ ቴክኒካል የመስክ እና ሁለገብ የምርምር ድጋፍ ሠራተኞች የምርምር ዕውቀታቸውን ለማሻሻል ያለመ ሲሆን፣ ስልጠናውም የምርምር ማሳ ላይ በሰፊው የተግባር ስልጠና ተሰጥቶበታል። የስልጠናው ዋና ዓላማ በማዕከሉ የምርምር ሥራ ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ሠራተኞች የዕውቀትና ክህሎት ክፍተቶችን በመሙላት የምርምር ውጤታማነትን ማሳደግ ነው።
ይህ ስልጠና በተለይ የምርምር ሥራዎችን በብቃት ለማከናወን የሚያስችሉ ዘመናዊ የምርምር ዘዴዎችን፣ የመረጃ አሰባሰብና ትንተና ቴክኒኮችን እንዲሁም የምርምር ግኝቶችን የማሰራጨት መንገዶችን ያካትታል።
በማዕከሉ የሚገኙ ልምድ ባላቸው ተመራማሪዎች የተሰጠው ይህ ስልጠና፣ ተሳታፊዎች በየዕለቱ በሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ የተሻለ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል። የሁለት ቀናት ቆይታውም ሠራተኞቹ ጥያቄዎችን እንዲጠይቁ፣ ልምዶችን እንዲለዋወጡ እና ከተመራማሪዎች ጋር በቀጥታ እንዲገናኙ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ምርምር ውጤቶችን በማሳደግና ለአ/አደሮዎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይህ ዓይነቱ የውስጥ አቅም ግንባታ ስልጠናም የማዕከሉን አጠቃላይ አፈጻጸም ለማሳደግና ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና አስተዋጽኦ ለማድረግ ወሳኝ እንደሆነ ተገልጿል።
02/04/2026
(ፓዌ፡-መጋቢት 24/2018 ዓ.ም) በፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ሁሉም ምርምር ሥራ ሂደት በዘጋጀዉ ስልጠና በስሩ ለሚገኙ ቴክኒካል የመስክ እና ሁለገብ የምርምር ድጋፍ ሠራተኞች ያላቸዉን የምርምር ዕዉቀት ለማሻሻል ላይ ያተኮረ ስልጠና በሚመለከታቸዉ የማዕከሉ ተመራማሪዎች በተከታታይ ሁለት ቀን የሚቆይ አቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
24/03/2026
በፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል የሆርቲካልቸር ምርምር ፕሮግራም በተለያዩ የአትክልትና የፍራፍሬ ሰብሎች ላይ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም አገር በቀል የሆኑ የፍራፍሬ ሰብሎችን ለቀጣይ ምርምር እንዲጠበቁና እንዲጠናከሩ የማቆያና የጥበቃ ተግባራትን በትኩረት ያከናውናል።
በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ከሚካተቱት አገር በቀል ፍራፍሬዎች መካከል “ትርንጎ” (Citron) ልዩ ትኩረት የተሰጠው ነው። ይህ ፍራፍሬ በከፍተኛ መጠን ትልልቅ ፍሬዎችን ማፍራት በመቻሉ ልዩ ባህሪ ያለው ሲሆን፣ እስከ 7.865 ኪ.ግ ክብደት፣ 43 ሴ.ሜ ርዝመት እና 47 ሴ.ሜ መጠነ ዙሪያ ያለው ፍሬ መሰብሰብ ተችሏል። ይህም በአካባቢው ለፍራፍሬ ምርት ልማት ከፍተኛ እድል እንዳለ የሚያመለክት ነው።
02/03/2026
(የካቲት 22/2018ዓ.ም) ለተለያዩ ሰብሎች ውሃን በልኬትና በጊዜ ሰሌደ በመስጠት የመስኖ ምርትና ምርታማነትን መጨመር እንደሚቻል የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ።
በፓዌ ወረዳ ቀ2 መ-30 ቀበሌ/ዳንጉር ጎጥ በፓዊ የግብርና ምርምር ማዕከል አማካኝነት የተሰሩ የመስኖ ምርምር ስራዎች ላይ ከአርሶ አደሮችና ማሳ ቅድመ- ማስተዋወቅ ሰርቶ ማሳያ ያለዉን ስንዴ፥ ሽንኩርትና እና ሽንብራ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር የመስክ ጉብኝት እና ምዘና አድርጓል፡፡
የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል ተወካይ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ታፈረ ሙሉአለም እንደገለፁት ምርምር ማዕከሉ በመተከል እና በአዊ ዞን በርካታ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የተሻለ ምርት የሚሰጡ የመስኖ ስንዴ ሰብል ዝሪዎችን በባለፉት አመታት በፊት ምርምር ማዕከሉ በመለየት ወረር ሁለት የተባለ ዝርያ ምርታማ መሆኑንና አሁን ደግሞ ዉሃ አሰጣጥ ሰሌዳ ማዉጣት የአ/አደሮች ጊዜና ጉልበት ይቆጥባል በማለት ገልፀዋል።
የፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል የአፈርና ዉሃ አያያዝ ምርምር የስራ ሂደት ተጠሪ የሆኑት ዶ/ር የኔሰው አሳየ እንደገለፁት በለስ ተፈሰስ የመሬቱ መልካዓ-ምደራዊ አቀማመጥ፥ የአፈር ባህርይ እና አካባቢው ከፍተኛ የሆነ የከረሰ-ምድርና ገፀ-ምድር የውሃ አቅም በመኖሩ ለመስኖ ልማት ምቹ ነው። በመሆኑም በምርምር የተደገፈ የመስኖ ቴክኖሎጂዎችና ምክረ-ሀሳቦችን ለተጠቃሚዎች ማስተዋወቅ የመሰኖ ምርታማነትን በማሻሻል የምግብ ሉዓላዊነትን እና ዋስትና ማርጋገጥ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
የመስኖና ዉሃ እቀባ ተመራማሪ የሆኑ አቶ ደመቀ ታመነ እና አቶ ተመስገን ፋንታሁን ሀገሪቱ በትኩረት እያሰራችበት ያለዉን የበጋ ስንዴ ትክክለኛዉን የመስኖ የጊዜ ሰሌዳ መጠቀም የመስኖ ዉሃን ከመቆጠብ በተጨማሪ ምርትና ምርታማነትን እንደሚጨምር አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም የመስኖና ዉሃ እቀባ ተመራማሪ ወ/ሮ አበባ ሀሰን ለሽምብራ ተጨማሪ ዉሃ በተፈለገዉ ጊዜ መስጠት ምርትና ምርታማነትን እንደሚጨመር አስረድተዋል፡
የፓዌ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ሃላፊ ተወካይ አቶ ሙሉጌታ አደነ እንደገለፁት ፓዌ ግብርና ምርምር ማዕከል አ/አደሮች ለተሻለ ምርት እንዲያገኙ የተደረገዉ የምርምር ስራ አበረታች መሆኑን በመግለጽ አ/አደሮች የተሰሩትን ቴክኖሎጅዎችን ተቀብለዉ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም ምርምር ማዕከሉ አረሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ እያበረከተ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ተሳታፊ አርሶ አደሮች አመስግነው በቀጣይ አዳዲስ ሌሎች የመስኖ ስራ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።