Demba Gofa Woreda Government Communication Affairs Office

Demba Gofa Woreda Government Communication Affairs Office

Share

በጎፋ ዞን ደምባ ጎፋ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽንጉዳዮች ጽ/ቤት

05/06/2026

ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ
**********************

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. ማለዳ ላይ፤ የመጀመሪያው የወገግታ ጭላንጭል በከፍታማዎቹ የኢትዮጵያ ተራሮች ላይ ፈንጥቆ ጨለማውን ሳይቀድ በፊት ኢትዮጵያውያን ረጃጅም ሰልፍ ተሰልፈዋል። በጅማ፣ በድሬዳዋ፣ በሐዋሳ፣ በባሕር ዳር እንዲሁም ስማቸው በዓለም አቀፍ የዜና ጋዜጣዎች ላይ ፈጽሞ ሊወጣ በማይችሉ ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ያሉ ወንዶችና ሴቶች፤ ወሳኝ ተግባር ለመፈጸም በሰልፍ ቆሙ። ድምፅ ሰጡ! ይህንን ታሪካዊ ኃላፊነት ለመወጣት ከሃምሳ አራት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ተመዝግበው ነበር። ይህ ቁጥር ከአንዳንድ ሀገሮች አጠቃላይ ሕዝብ ቁጥር በላይ ነው። ይህ ምርጫ እውነተኛ ስለመሆኑ ጥያቄ ለሚያነሣ ለማንኛውም አካል ግልጽ እና የማያሻማ ምላሽ ሰጥቷል!

‎የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት
‎የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ52,000 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ከ50,188 በላይ የሚሆኑት በሰዓቱ ተከፍተው ቀኑን ሙሉ መራጮችን ሲያስተናግዱ እንደነበር አረጋግጧል። ከ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተወጣጡ ከ10,438 በላይ ዕጩዎች እና 80 የግል እጩዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤት ወንበሮችን ለማሸነፍ ተወዳድረዋል። ይህ በማንኛውም ሊለካ በሚችል መሥፈርት በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቁ እና በውሳኔ አሰጣጥም ሆነ በአስተዳደራዊ ረገድ እጅግ በረቀቀ ሁኔታ ተግባራዊ የተደረገ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የታየበት ኩነት ነበር።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ክቡር ኡሁሩ ኬንያታ የሚመሩትና ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ታዛቢዎችን ያቀፈው የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን ምርጫውን “ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በሰፊው በሚደግፍ ሕጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ ውስጥ የተካሄደ” ሲል ገምግሞታል። በቀድሞዋ የኡጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ክብርት ዶክተር ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ የሚመራው የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት፥ በታዘቡባቸው ጣቢያዎች ሁሉ የምርጫ ሳጥኖች በትክክል የታሸጉ መሆናቸውን፣ የፓርቲ ወኪሎች በሂደቱ በሙሉ መገኘታቸውን እንዲሁም ምርጫው አስደናቂ ተቋማዊ፣ አስተዳደራዊና የቴክኖሎጂ ዕድገትን ያሳየ መሆኑን አረጋግጧል። የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ይሄንን ምርጫ «የበርካታ አዳዲስ ምዕራፎች ምርጫ» ሲል ሰይሞታል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በድምፅ መስጠት ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልተመለከተ አረጋግጧል። የሲቪክ ማኅበረሰብ ታዛቢዎች ጥምረት በምርጫ ቦርድ እውቅና ከተሰጣቸው 55 ድርጅቶች 65,299 የታዛቢዎችን በመላ ሀገሪቱ ያሠማራ ሲሆን፥ 99 በመቶ የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ያለምንም ዕንቅፋት የመታዘብ ዕድል ማግኘቱን አረጋግጧል። እነዚህ ተዓማኒነት ያላቸው ሀገራዊ እና አኅጉራዊ ተቋማት ያደረጓቸው ግምገማዎችና የሰጧቸው እውነተኛ ፍርዶች ናቸው። እነዚህ ለአፍሪካ ጥላቻ ካላቸው ወይም የአፍሪካን ዴሞክራሲ በውጫዊ መሥፈርቶች ከሚለኩ ተቋማት የተደመጡ ድምፆች አይደሉም።

‎አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተንታኞች ይሄንን ምርጫ እንደ ንግሥና በዓል አድርገው ያቆሸሹት ሲሆን ውጤቱም አስቀድሞ የተወሰነ ድራማ እንደነበር አድርገው ሊያቀርቡት ሞክረዋል። እነዚህን መግለጫዎች ከእውነታው ፈጽሞ የራቁ፣ በጥናትና ትንተና ላይ ያልተመሰረቱ እንዲሁም ነፃና የታሰበበት ዴሞክራሲያዊ ምርጫቸውን በኩራት ላደረጉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ክብር የማይሰጡ በመሆናቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሙሉ በሙሉ የማይቀበላቸው መሆኑን ያረጋግጣል። አስቀድሞ የተወሰነ ውጤት ቢኖር ኖሮ፤ ከ37 የአፍሪካ ሀገሮች የተወጣጡ 83 ገለልተኛ ታዛቢዎችን፣ 65,299 የሀገር ውስጥ የሲቪል ማኅበረሰብ ታዛቢዎችን ወይም 1,100 ዕውቅና የተሰጣቸውን ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች መጋበዝ ባላስፈለገ ነበር።

‎ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ሀገራዊ ምርጫ ለተሳተፉ የኢትዮጵያ ዜጎች፣ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ላሠማራቸው ከ350,000 በላይ ኃላፊዎች፣ ሂደቱን ለጠበቁት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ኢትዮጵያ ለዴሞክራሲ ግንባታ መጎልበት እና ለሂደቱ መሳካት ያላትን ቁርጠኝነት ላረጋገጡት የአፍሪካ እና ቀጣናዊ የታዛቢ ቡድኖች ምስጋናቸውን ያቀርባሉ!

‎ስለ ኢትዮጵያ ልማት
‎ኢትዮጵያውያን ግንቦት 24 2018 ዓ.ም ውሳኔያቸውን ሲያስቀምጡ፣ ሀገራቸውን በፍጹም የዴሞክራሲ ባህል ውስጥ ለማንበር ነው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ባላት ጸጋ ልክ የሚያስፈልጋትን ሁለንተናዊ ልማት በፍጥነት እውን የማድረግ ባህል እንዲቀጥል ሕዝባችን ተናግሯል።

‎ባለፉት ዓመታት የታየው እውነት እንደሚያሳየን የኢፌዴሪ መንግሥት የተስፋ ቃል መንግሥት አልነበረም። ይልቁንም በተጨባጭ የሚታዩ ውጤቶች የተመዘገቡበት ውጤት ተኮር መንግሥት ሲሆን፤ እነዚህም ውጤቶች በግልጽ የሚታዩ ናቸው። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት የ9.2 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፥ ይሄም በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ካስመዘገቡ ኢኮኖሚዎች አንዱ ያደርገዋል። ይሄንን መነቃቃት መሠረት በማድረግ በ2018 በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ዕድገቱ 10.2 በመቶ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል። ዕድገቱ ግብርናን፣ ኢንዱስትሪንና የአገልግሎት ዘርፎችን በከፍተኛ ደረጃ ያካተተ ሰፊ መሠረት ያለው ቢሆንም፥ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን ኢንዱስትሪው ለዕድገቱ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ሆኖ እየመጣ ይገኛል። ይሄም መንግሥት ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለዕሴት ጭማሪና ለውጭ ገበያ ተኮር ምርቶች የሰጠውን ቀጣይነት ያለው ትኩረት ያሳያል።

‎እነዚህ ውጤቶች እንዲሁ ግምቶች ብቻ ሳይሆኑ፥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የ100 ቀናት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሥርዓት አማካኝነት ክትትል የሚደረግባቸው የተጠያቂነትና የታቀደ አመራር ፍሬዎች ናቸው። አጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ 20 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ይህም ከ2016 ዓ.ም. ወዲህ የ100 በመቶ ገደማ ጭማሪ አሳይቷል። የዋጋ ግሽበትም ወደ ታች ማሽቆልቆሉን በመቀጠል አሁን ላይ ወደ አንድ አሐዝ ደረጃ እየተቃረበ ይገኛል፤ ይሄም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በቤተሰቦችና በንግዶች ላይ ከባድ ጫና ፈጥሮ ከነበረው ባለ ሁለት አሐዝ የዋጋ ግሽበት አንጻር ትልቅ መሻሻል ነው። ይህ ስኬት የተመዘገበው ዓለም አቀፍ የኃይል አቅርቦትና ሌሎች ስትራቴጂካዊ ቁሳቁሶችን ገበያ ያናጋው የመካከለኛው ምስራቅ ወቅታዊ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ጨምሮ፣ ውጫዊ ጫናዎች በነበሩበት ወቅት ነው።
‎የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ከተጀመረ ወዲህ መንግሥት ከውጭ ምንጮች ምንም ዓይነት አዲስ የንግድ ብድር ስምምነት ያላደረገ ሲሆን፥ ይሄም የሀገሪቱን የብድር ዕዳ ጫና በከፍተኛ ሁኔታ አቅልሎታል። ከእነዚህ ቁጥሮች በስተጀርባ ኢትዮጵያውያን በዓይናቸው የሚያዩትና በእጃቸው የሚዳስሱት ተጨባጭ ለውጥ አለ። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለመኖሪያ ቤቶች፣ ለንግድ ተቋማትና ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጨ ይገኛል። ይህ ግድብ በራሳቸው በኢትዮጵያውያን የተደገፈ፣ በኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች የተገነባና ቀጣይነት የነበረውን ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ የተጠናቀቀ ነው። ከሃይድሮ ፓወር ጎን ለጎን፥ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሚገኘውን የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ እና በአርሲ ዞን የሚገኘውን የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፤ በመሳሰሉ ሥራዎች የታዳሽ ኃይል አቅርቦቷን እያሰፋች ሲሆን፥ ይህም የቀጣናዊ ኢነርጂ ትብብርን እያሳደገ የብሔራዊ ኃይል አቅርቦት መረቡን የመቋቋም ዐቅም ያጠናክራል። በአፍሪካ አህጉር ታሪክ ውስጥ ትልቁ የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት አንዱ የሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው ተጀምሯል። እነዚህ ምኞቶች አይደሉም፤ ተጨባጭ ሐቆች ናቸው።

‎ግብርና፣ አምራች ኢንደስትሪና ቴክኖሎጂ
‎በግብርናው ዘርፍ፣ የመንግሥት የምግብ ሉዓላዊነት አጀንዳ ወቅታዊ ለውጦችን ሳይሆን መዋቅራዊ ውጤቶችን እያስገኘ ቀጥሏል። በሶማሌ ክልል የጎዴ ዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካን ለመገንባት ከአሊኮ ዳንጎቴ ግሩፕ ጋር የተፈረመው አጋርነት የዘመኑ ጉልህ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንቶች አንዱ ማረጋገጫ ነው። ፋብሪካው በዓመት 3 ሚልዮን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ የማምረት አቅም እንዲኖረው ታቅዶ እየተገነባ ሲሆን፥ ይሄም ኢትዮጵያን በዓለም ትላልቅ ማዳበሪያ አምራች ሀገራት ተርታ ያሰልፋታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. የፕሮጀክቱን የግንባታ ሂደት በጎበኙበት ወቅት እንደገለጹት፤ “ይህ ፕሮጀክት በግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በምግብ ዋስትና፣ በኢንዱስትሪ ዕድገትና በኢኮኖሚ ራስን መቻል ላይ የተደረገ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው” ብለዋል። አስተማማኝ ባልሆነና ውድ በሆነ የማዳበሪያ አቅርቦት ለረጅም ጊዜ ለተገደቡት ኢትዮጵያውያን አምራቾች የዚህ ፕሮጀክት ፋይዳ ፈጣንና ተጨባጭ ነው።

ከዚህ ምርጫ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በነገሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ ምርቃት ላይ ሲገኙ የታየው ተምሳሌትነት ለቦረና ሕዝብ ትልቅ ትርጉም ነበረው። ይህ ዞን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅበት ስም የሀገርን አንገት ያስደፋ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ሲሆን፤ እርሱም ድርቅ ነው። ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የዝናብ መጥፋት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶችን የገደለ፣ ቤተሰቦች ለውኃ ፍለጋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን እንዲጓዙ ያስገደደ፣ እንዲሁም በእነዚህ የግጦሽ መሬቶች ላይ ለዘመናት ራሳቸውን ችለው የኖሩ ማኅበረሰቦችን ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ እጅ እንዲዘረጉ አድርጎ ነበር። ዓለም የሚያውቃት ቦረና እርሷ ነበረች። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንቦት ወር ጉብኝት ግን የተለየ ታሪክ አሳይቷል። አሁን ላይ ለአርብቶ አደር ማኅበረሰቦችና ለከብቶቻቸው ንጹሕ ውኃ እያቀረቡ ያሉትን የውኃና የመስኖ መሠረተ ልማቶችን የገመገሙ ሲሆን፥ ከጥቂት ዓመታት በፊት አቧራ ብቻ በነበረው መሬት ላይ የክላስተር እርሻዎችን ጎብኝተዋል፤ በያቤሎ የባህል ማዕከል መርቀዋል፤ እንዲሁም በአየር ንብረት ሁኔታዎች ምክንያት ቀድሞ ተገልሎ ለነበረው ቀጣና ዓመቱን ሙሉ ትስስር የሚፈጥር አውሮፕላን ማረፊያ መርቀው ከፍተዋል።

‎የአምራች ዘርፉም ተመሳሳይ የለውጥ ታሪክ አለው። በግንቦት 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 4ኛው ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ላይ፤ መንግሥት ለአራት ዓመታት የተመዘገበውን ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ መስፋፋት ውጤቶች አቅርቧል። የአምራች ዘርፉ የግብአት አቅርቦት በዓመት 9 ሚልዮን ቶን ወደ 15 ሚልዮን ቶን አድጓል። የምርት አቅም አጠቃቀም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማለቱን፣ የማኑፋክቸሪንግ ዕድገት ከ4.8 በመቶ ወደ 10.7 በመቶ ማደጉን፣ እንዲሁም ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበው ፋይናንስ ከ8.1 ቢልዮን ብር ወደ 50 ቢሊዮን ብር ማደጉን ያሳያል። እነዚህ ስኬቶች በሀገር ውስጥ ምርት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተንጸባረቁ ይገኛሉ። ኤክስፖው በተጠናቀቀ በሃያ ቀናት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ተጠናቆ ከ80 በመቶ በላይ ጥሬ ዕቃውን ከሀገር ውስጥ የሚያገኘውን ግዙፍ የኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት «ግራንዲዩር የሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ» ፋብሪካን በሞጆ ከተማ መርቀዋል። ቀደም ሲል በገቢ የሴራሚክ ምርቶች ላይ ጥገኛ የነበረችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሴራሚክ ምርቶችን ከውጭ ማስገባት ሙሉ በሙሉ ለማቆምና ለውጭ ገበያ የሚሆን ምርት ለማስፋፋት እየተዘጋጀች ትገኛለች።

‎በቴክኖሎጂው ዘርፍም፥ ዘመናዊ ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ በዳታ፣ በፈጠራና በዲጂታል ሥርዓቶች የሚወሰን መሆኑን በመገንዘብ፥ መንግሥት ኢትዮጵያን ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የኢንዱስትሪ 5.0 ማሕቀፎችን ቀድመው ከተገበሩ ሀገራት ተርታ እያሰለፋት ይገኛል።

‎የጽንፈኝነትን ፖለቲካ ውድቅ ማድረግ
‎በኦነግ ሸኔ ዐማጽያን በንጹሐን ዜጎች ላይ በተለይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ዒላማ ተደርገው የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ፤ የቤተሰብ እና የወዳጆቻቸውን ሕይወት ላጡ፣ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው እና የቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው በአርሲ ዞን ለሚገኙ ወገኖቻችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ መንግሥት ስም የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻሉ።

እነዚህ ጥቃቶች የሀገሪቱን ብሔራዊ ዕድገት ለማደናቀፍ ከሚሹ አካላት፣ በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ አማፂ ቡድኖች እና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ጥላቻ ካላቸው የውጭ ኃይሎች ጋር በጥምረት የተከናወኑ ሲሆኑ፤ ዓላማቸውም በኢትዮጵያ አለመረጋጋትንና የምርጫ መስተጓጎልን ለመፍጠር ሲደረግ የነበረ የጥፋት ውጥን ተከታይ ነው። መንግሥት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ያለ አንዳች የፀጥታ ችግር ፍትሐዊና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ልዩ ትኩረትና ዝግጅት በማድረግ በቁርጠኝነት ሲሠራ ቆይቷል። በሌላ በኩል የጥፋት ኃይሎች ከባዕዳን ጋር 'ፅምዶ' የሚል ቁርኝት በመፍጠር ዕኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ሰፊ የጥፋት ዝግጅት ሲያድርጉ ቆይተዋል፣ ሀገራዊ ምርጫው እንዳይከናወን ሰፊ ርብርብ አድርገዋል። በተጨባጭም በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት የዜጎችን የመምረጥ መብትና ነጻነት ለመጋፋትና ለማደናቀፍ አለን የሚሉትን የጥፋት እጅ ዘርግተዋል።
‎እነዚህ የጠላት ኃይሎች በመደጋገፍና በመናበብ ዐመፅና ሁከት ለማነሳሳት፣ ከተሞችን በሽብር ጥቃት ለማወክ፣ በመንገዶች የደፈጣ ጥቃት በመፈጸም እንቅስቃሴ ለመገደብ እና በተወሰኑ አካባቢዎች ዒላማ አድርገው ነጥሎ ለማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል። እንደ ማሳያ የጦር መሣሪያ፣ ተተኳሾችንና ሌሎች ሎጀስቲክሶችን በድጋፍ በማቅረብ በደቡባዊ ትግራይ በሚገኙ አዋሳኝ የአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትንኮሳ ፈጽመዋል፣ በአማራ ክልል ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን እና ወልድያ ከተሞችን ጨምሮ በክልሉ ዋና ዋና ከተሞች እና ሲቪሎች ላይ ዒላማ በማድረግ ያካሄደው የሽብር እንቅስቃሴና ዝግጅት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ባደራጃቸው የኅቡዕ ሴሎች አማካኝነት በተመረጡ አከባቢዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ተንቀሳቅሰው የነበረ ቢሆንም ይሄን የጥፋት ሴራ እና ድርጊት እንዲከሽፍ ማድረግ ተችሏል።

‎በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል የሸኔ ሽብር ቡድን ከጽንፈኛው ፋኖ ታጣቂ ቡድን ጋር በመናበብ በአንዳንድ አካባቢዎች መንገዶችን በመዝጋት እንቅስቃሴ ለማስቆምና ለማስተጓጎል ፍላጎት የተንቀሳቀሰ ቢሆንም በጸጥታ ኃይሉ በተወሰደበት የተጠናከረ እርምጃ ፍላጎቱን ማሳካት አልቻለም። ቡድኑ በፀጥታ ኃይሉ የተወሰደበትን ርምጃ መቋቋም ባለመቻሉ እና ፍላጎቱን ማሳካት ባለመቻሉ ስስ ዒላማዎች ላይ ያተኮረ ርምጃ በመውሰድ የሃይማኖት እና የብሔር ግጭት ለመቀስቀስ በማለም በአርሲ ዞን አሰኮ እና አካባቢው ጥቃት በመፈጸም ሁሉን አይነት የጥፋት ርብርብ ያደረገ ቢሆንም ሁኔታውን በመቆጣጠር ፀጥታ ኃይላችን በእነዚህ ኃይሎች ላይ የተቀናጀ ርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

መንግሥት መሰል ሥጋቶችን በንቃት በመከታተል ላይ ሲሆን፣ በምርጫው ወቅትም በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀነባበሩ ተመሳሳይ ዕቅዶችን በስኬት ማክሸፍ ችሏል። በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን፤ ፍርሃትና ክፍፍልን ከሚያጎሉ የሚዲያ ዘመቻዎች ጋር በማስተሣሠር የተቀነባበረው ይህ እኩይ ተግባር፤ በመንግሥት የደኅንነት መዋቅርና ኦፕሬሽኖች አማካኝነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲስተጓጎል ተደርጓል። ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ ክፍፍልን ለመዝራት የኃይል ጥቃትን እና ውድመትን እንደ መሣሪያ የሚጠቀሙ አካላት በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በግልጽ ሊወገዙ ይገባል። መሰል ተግባሮች በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የወደፊት ዕድል እንደሌላቸው ለማሳየት የተቀናጀ ብሔራዊ ምላሽ በመስጠት ወሳኝ ርምጃዎችን ይቀጥላል።

‎በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙ አካላት፣ ድርጊታቸውን ምክንያታዊ ለማስመሰል ምንም ዓይነት የፖለቲካ ንግግር ቢጠቀሙ፤ ወሳኝ ዓላማን እያሳኩ ሳይሆን ወንጀል እየፈጸሙ ነው። የፖለቲካ ቅሬታዎች በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት፣ በብሔራዊ ምክክር ሂደት እና በዴሞክራሲያዊ ተቋማት አማካኝነት መፍትሔ ሊያገኙ የሚችሉ እና ሊያገኙ የሚገባቸው ናቸው።


ጽንፈኝነት ግን በኢትዮጵያ ምድር ፈጽሞ ቦታ የለውም!

EBC

Photos from Demba Gofa Woreda Government Communication Affairs Office's post 05/06/2026

‎የክልሉ ጤና ቢሮ ክልል አቀፍ የህጻናት የኩፉኝ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ መርሐ ግብር በጌዴኦ ዞን ራጴ ወረዳ አስጀመረ

ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ክልል አቀፍ የህጻናት የኩፉኝ በሽታ መከላከያ የክትባት ዘመቻ መርሐ ግብር በጌዴኦ ዞን ራጴ ወረዳ በዛሬው ዕለት አስጀምሯል ።

‎በመርሃግብሩ የተገኙት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ መና መኩሪያ ከቅድመ እስከ ድህረ ወሊድ በህክምና አገልግሎት ወላድና ልጅን ከሞት ለመታደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

‎በቅድመ ወሊድ የህክምና አገልግሎት ወቅት ለእናት እና ለተፀነሰው ልጅ ጠቃሚ የሆነ ክትባት፣ መድሃኒት እና የተለያዩ ምርመራዎች እንደሚደረጉ የጠቀሱት አቶ መና ይህም ለወላድ እናትና የተወለደው ህጻን ጤናማ ብቁ ዜጋ እንዲሆን ከፍ ያለ አስተዋፅዖ እንዳለው ተናግረዋል።

የእናቶችን እና የህጻናት ሞት ለመቀናስ እየተሰሩ ካሉ ስራዎች አንዱ የክትባት ዘመቻ ሲሆን በዚህም በጨቅላ ህጻናት ህይወት አድን ሥራ አበረታች ውጤት እየታየ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለዋል ።

‎የክትባት አሰጣጡ ጥራቱን የጠበቀ ከመሆኑ የተነሳ የኩፉኝ በሽታ በክልሉ በዚህ ዓመት እንዳልተከሰተ ያስረዱት ምክትል ኃላፊው በዘመቻውም ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ስርጭቱ እንዲካሄድ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን እና ባለድርሻዎች ርብርብ ኢንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።

‎የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገደቾ
‎በበኩላቸው መንግስት የነገውን ሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማዳን በሚያደርገውን የህክምና አገልግሎት ህብረተሰቡ በመገንዘብ ህጻናትን እንድያሰከትብ ጥሪያቸውን አቅርበዋል

‎የራጴ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንስ ሕነስ
‎የኩፉኝ በሽታ ክትባት ዕድሜያቸው ከ6 ወር እስከ 10 ዓመት ለሆናቸው ህጻናት ከግንቦት 28- ሰኔ 01/2018 ዓ.ም በጊዜያዊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎች ፣ በት/ቤቶች እንዲሁም በጤና ተቋም በዘመቻ ይሰጣል ብለዋል ።

‎የወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደጀነ ሽብሩ እንደ ወረዳ ባለፉት ለአንድ ዓመት ያህል የኩፉኝ በሽታ አለመከሰቱን ገልጸው አሁን ላይ በታዩ ናሙና እንደ ወረዳው 29,399 ህጻናት ለማስከተብ ታቅዶ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አመላክተዋል ።

Photos from Demba Gofa Woreda Government Communication Affairs Office's post 05/06/2026

የጎፋ ዞን ልማት ማህበር በዋና መስሪያ ቤት ጎዝዳ የማህበረሰብ መድኃኒት መደብር በሣውላ ከተማ‎ መክፈቱን ገለፀ።

‎ሣውላ፦ግንቦት 28/2018 ዓ/ም

‎የጎፋ ዞን ልማት ማህበር ዋና መስሪያ ቤት ጎዝዳ የማህበረሰብ መድኃኒት መደብር በሣውላ ከተማ የቦርድ አመራሮችና አባላት በተገኙበት መርቆ በመክፈት ለአገልግሎት ማብቃቱን የተገለፀው።

‎የጎፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ምናሴ ኤልያስ በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የጎፋ ዞን ልማት ማህበር ከዞኑ ምስረታ ጋር እኩል የተመሰረተ ቢሆንም የዕድሜውን ያክል ለውጥ ለማስመዝገብ የተቀናጀና የትብብር ስራዎች የተሰራ ባለመሆኑ የውስጥ ሪፎርም ማድረግ በማስፈለጉ ማህበሩን ለማሻገር በአዲስ አመራር ተዋቅሯል ብለዋል።

‎አቶ ምናሴ ኤልያስ አያይዘው በአዲስ መልክ የተመረጡ የጎፋ ልማት ማህበር አመራሮች ማህበሩ የተቋቋመበት ዓላማ የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር ትልልቅ የልማት ስራዎችን በማስጀመር ዛሬ በሣውላ ከተማ ጎዝዳ የማህበረሰብ መድኃኒት መደብር ሙሉ መዳኃኒቶችን በማስገባት ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል በማለት ገልፀዋል።

‎አክለውም የጎዝዳ የመድኃኒት መደብሩ መዳኃኒቶችን ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ በጎፋ ዞን የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ሆኑ ሌሎች ያለ እንግልት ወደ መደብሩ በመምጣት ገዝተው ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ገልፀዋል።

‎የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ም/ኃላፊ ወ/ሮ አሚናት ሰይድ በበኩላቸው የጎፋ ዞን ልማት ማህበር ለማህበረሰቡ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የዛሬው ጎዝዳ የማህበረሰብ መዳኃኒት መደብር ማሳያ ነው ብለዋል።

‎አያይዘውም በጤናው ዘርፍ ለማህበረሰብ ተጠቃሚነት ማህበራት ወደ መስኩ ለመስራት የሚያደርጉት ስራ የመንግስትን የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት በማስወጣት ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ በመሆኑ የጎፋ ልማት ማህበር ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ልመሰገን ይገባል በማለት ተናግረዋል።

‎የጎፋ ዞን ልማት ማህበር ስራአስክያጅ ኢንጂነር ነፃነት ገመዳ እንደገለፁት የጎፋ ዞን ልማት ማህበር ከዚህ ቀደም በየመዋቅሮች ሰባት የማህበረሰብ መዳኃኒት መደብር እንደከፈተ ተናግረው ዛሬ በጎፋ ልማት ማህበር ዋና መስሪያ ቤት ግቢ ጎዝዳ የማህበረሰብ መዳኃኒት መደብር ለስምንተኛ ጊዜ መክፈቱን ገልፀዋል።

‎አክለውም የጎዝዳ መድኃኒት መደብር በሚከፈትበት ወቅት የመድኃኒት እጥረቶች እንዳያጋጥሙት ከኢትዮጵያ ጤና ሚንስቴር ጋር በመተባበር የዕውቅና ምዝገባ በማስደረግ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ የጤና ስራዎችንና ቁሳቁሶችን ለማህበረሰባችን በተመጣጣኝ ዋጋ እናቀርባለን ብለዋል።

‎በመጨረሻም ከተሳታፊ አካላትና አመራሮች ማህበሩን በዘላቂነት ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውና የተጀመሩ ስራዎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ሃሳብ አስተያዬቶች ተሰጥተውባቸው መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።

Photos from Demba Gofa Woreda Government Communication Affairs Office's post 05/06/2026

በክልሉ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተቀናጀ ተፋሰስ ልማትና በመሬት አስተዳደር ዘርፎች የሚታይ ውጤት መመዝገቡ ተገለጸ

ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ፥ በአየር ንብረት አፈፃፀምና የመሬት አያያዝ ፕሮግራም (CALM P4R) የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠቃለያ እና የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወር ፋይናንሻል አፈፃፀም እና የሂሳብ መዝጊያ መድረክ በአርባምንጭ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የፕሮግራሙ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አብዮት ዘሪሁን፥ የፕሮግራሙ የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወር ፋይናንሻል አፈፃፀም ሪፖርት እና ፕሮግራሙ ከመዘጋቱ በፊት መፈጸም የሚገቡ ዝርዝር ተግባራትን የሚያሳይ መመሪያ የያዘ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፥ ፕሮግራሙ በክልሉ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ 67 በመቶ እና በገጠር መሬት አስተዳደር ሥራ ላይ 33 በመቶ ውጤት ተሰጥቶት የሚተገበር ፕሮግራም መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮግራሙ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተቀናጀ የተፋሰስ ልማትና መሬት አስተዳደር ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ክልሉ በይፋ ከተመሠረተ በኋላ ፕሮግራሙ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ጀምሮ ባለፉት ሦስት ዓመታት በ65 ወረዳዎች ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በመመደብ በርካታ የሚታዩ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ገልጸዋል።

የፕሮግራሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ መዝጊያ ጊዜ ከመጠናቀቁ በፊት ለፕሮግራሙ የተመደበው ሀብት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሁሉም መዋቅሮች ጥራት ያለውን ሪፖርት ማቅረብ፣ ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር፥ የክትትልና ቁጥጥር ስርዓትን በማጠናከርና የማጠቃለያ ሪፖርት በበላይ ኃላፊ እና በውስጥ ኦዲተር ተፈርሞ ተረጋግጦ ማቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊና የመንግስት ፋይናንስ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ምህረቱ አሰፋ፥ ፕሮግራሙ ስድስት ዓመታትን በሥራ ላይ ቆይቶ የመጀመሪያ ምዕራፍ በያዝነው ዓመት መጨረሻ ላይ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

የፕሮግራሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ መዝጊያ ከመጠናቀቁ በፊቱ ምንም አይነት ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች እንዳይኖሩ ክትትል የተደረገበትን ደረጃ በመገምገም ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፥ ፕሮግራሙ የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የአርሶአደሩን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ የበኩሉን ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።

በመድረኩ የቢሮው ምክትል ኃላፊዎችን ጨምሮ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የተወጣጡ የፋይናንስ መምሪያና ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም ፎካሎች ተሳታፊ ሆነዋል ሲል የክልሉ ፋይናንስ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል ።

Photos from Demba Gofa Woreda Government Communication Affairs Office's post 05/06/2026

የ7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በማስመልከት የዞኑ ፖሊስ ማናጅመንት አካላት ስምሪት የማጠቃለያ ግብረ-መልስ መድረክ አካሂዷል ።

ሳውላ ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

7ተኛውን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በሠላም በነፃና በታማኝነት እንድጠናቀቅ የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሲያከናውናቸው የቆየያቸውን የጸጥታና ደህንነት ሥራዎች በመገምገም ከዞኑ ፖሊስ ማናጅመንት አካላት ጋር የማጠቃለያ ግብረ-መልስ ተካሂዷል ።

በማጠቃለያው መድረኩ ላይ የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ም/ኢ/ር ሀይሉ ወዳጆ እና የመምሪያው ፖሊስ ማናጅመንት አካላት ተገኝተው የነበረውን አፈፃፀም በዝርዝር የገመገሙ ሲሆን ለቀጣይ ሥራዎች አቅጣጫ የሚጠቁም ሰፊ ግብረ መልስ ሰጥተዋል ።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ተወካይ ም/ኢ/ር ሀይሉ ወዳጆ በማጠቃለያው ላይ የምርጫው ሂደት ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጸጥታ ሀይሉ ሌሊትና ቀን በቁርጠኝነት መስራቱን ተናግረዋል ።

ህዝቡ ያለምንም ሥጋትና ፍርሃት ድምምፃቸዉን እንድሰድሰጡ የዴሞክራሲያዊ መብቱ እንድከበር ፖሊስ የነበረው ሚና ከፍተኛ እንደነበረ ጠቁመው ።ላሳየው ዝግጁነትና ላስመዘገው ስኬት ማናጅመንቱንና መላው የፖሊስ ሠራዊቱን አመስግነዋል ።

የማናጅመንቱ አካላት በበኩላቸው በምርጫው ወቅት ያጋጠሙ ጠንካራ ጎኖችንና ክፍተቶችን በዝርዝር ያስቀመጡ ሲሆን የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን ይበልጥ በማጠናከር በቀጣይ በሚሰሩ የህግ ማስከበር ሥራዎች ላይ መሰራት እንደሚገባ ገልጸዋል ።

ይህ የምርጫ ሂደቱ ሠላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ ፀጥታ መዋቅሩ ካለው ቅንጅታዊ አሰራርና ከህዝቡ ከፍተኛ ትብብር የመነጨ ነው ያሉት ም/ኢ/ር ሀይሉ ወዳጆ የተገኘው ሠላም ቀጣይነት እንዲኖረው ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ያለውን አጋርነት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል ።

በመጨረሻም የምርጫው ማጠቃለያ ግብረ መልስ መድረክ የፀጥታ ስምሪቱን ስኬታማነት ያረጋገጠ መሆኑ ተገልጾ የዞኑን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ለዚህ ስከታማነት ‎የሰላምና ደህንነት ስራን በቆራጥነት የተወጣችሁ አጠቃላይ የዞኑ ፖሊስ አመራሮችና አባላት፣ የክልሉ አድማ ብተና አመራርና አባላት፣ ብሐራዊ መረጃ ደህንነት፣ የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊዎችና የ12 ቱ ፖሊስ መዋቅሮች እና ባለድርሻ አካላት፣ የሚሊሻ ጽ/ቤት ኃላፊ እና ባለሙያዎች፣ በአጠቃላይ በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩትን አካላት ፖሊስ መምሪያው ምስጋናውን አቅርቧል ።

ምንጭ የጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ ኢንዶክቴሪነሽና ህዝብ ግንኙነት ዲቭዥን

Photos from Demba Gofa Woreda Government Communication Affairs Office's post 05/06/2026

በደምባ ጎፋ ወረዳ 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ አፈፃፀም ከአጠቃላይ አመራሩ ጋር የማጠቃለያ ግምገማ መድረክ አካሄደ

ሳውላ፣ ግንቦት 28/2018 ዓ.ም (ደምባ ጎፋ ወረዳ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት)

በደምባ ጎፋ ወረዳ የ7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ አፈፃፀም ከአጠቃላይ አመራሩ ጋር የማጠቃለያ ግምገማ መድረክ አካሂዷል።

መድረኩን የደምባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ደበላ እና የወረዳው ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ እውነቱ ጎንጋሻ በጋራ መርተዋል።

በመድረኩ ላይ የደምባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ያዕቆብ ደበላ እንደገለጹት፣7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ያለምንም የደኅንነት ስጋት ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት ከፍተኛ ተጋድሎ ለሁሉም አካላት ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

አቶ ያዕቆብ አክለውም፣በ7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ለህዝቡ የተገቡ የመሠረተ ልማት ቃልኪዳኖችን ለመፈጸም አመራሩ ከፍተኛ መስዋዕትነት እንደከፈለ ገልጸዋል።

በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በብዙ ተግዳሮቶች መካከል በወረዳው ሰላማዊና በተሳካ ሁኔታ መካሄዱ የወረዳ አመራሮችና የመራጩ ህዝብ ትብብር ውጤት ነው ስሉ አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የደምባ ጎፋ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ እውነቱ ጎንጋሻ እንደገለጹት፣የምርጫው በሰላም መጠናቀቅ ለወረዳው ትልቅ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

አክለውም ህዝቡም በችግሮች መካከል ሆኖ እንኳን ለአመራሩ እምነት ሰጥቶ፣የተገባው ቃል በተግባር መፈፀሙን ተናግረዋል።

በቀጣዩ ትኩረት የተጀመሩ የልማት፣የመልካም አስተዳደርና የሰላም ማስከበር ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሆነም አስረድተዋል።

እንዲሁም የምርጫው ማጠቃለያ ግምገማ ያሉትን ጥንካሬዎች ለማስቀጠልና በሂደቱ የታዩ ክፍተቶችን ለማረም መነሻ መሆኑ አስገንዝበዋል።

ምርጫውን ማሸነፍ የተቻለው በአጠቃላይ ሀገራዊ ለውጦችን በማሳየትና ከዚህ በፊት የተሰሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ህዝቡ በማየቱና በማመኑ እንደሆነ አብራርተዋል።

እንደወረዳ ያልተሰሩ ወይም ያልተጠናቀቁ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በቀጣይ ጊዜ ለማከናወን ከህዝቡ ጋር የተደረሰ መግባባት ወረዳው ሙሉ ድምፅ እንዲያገኝ አስችሎታል ተብሏል።

በመጨረሻም፣በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሳካት የታቀዱ የተቋማት ተግባራት አፈፃፀም ግምገማ እንዲካሄድ፣ እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅዶች በአስቸኳይ ተገምግመው በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲቀርቡ መመሪያ መሰጠቱ ተጠቁሟል።

በመድረኩ ላይ የደምባ ጎፋ ወረዳ አስተባባሪ አካላትና አጠቃላይ አመራሮች ተገኝተዋል።

በሀብታሙ ዙዛ

05/06/2026

በዞኑ በበጀት ዓመቱ የጤና መሠረተ ልማት መነቃቃት የማህበረሰቡን የጤና እና ኢኮኖሚ የመታደግ ስኬት

Photos from Demba Gofa Woreda Government Communication Affairs Office's post 04/06/2026

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ከወረዳ አስተዳዳሪዎችና ከከተማ ከንቲባዎች ጋር የ7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ አፈፃፀም አጠቃላይ ሁኔታን በመገምገም እንዲሁም በ120 ቀናት ዕቅድ የቀሩ ተግባራት ላይ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።

ግንቦት 27/2018 ዓ.ም

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ከወረዳ አስተዳዳሪዎችና ከከተማ ከንቲባዎች ጋር የ7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ አፈፃፀም አጠቃላይ ሁኔታን በመገምገም እንዲሁም በ120 ቀናት ዕቅድ የቀሩ ተግባራት ላይ ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ወቅት ዋና አስተዳዳሪው 7ኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት በሰላማዊ፣ እና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልጸው፣ ለዚህ ስኬት የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ያደረጉትን ጠንካራ ሥራ አድንቀው አመስግነዋል።

አመራሩ በምርጫው ሂደት ያሳየውን ቅንጅታዊ አሠራር፣ የችግር ፈቺነት እና የውጤት ተኮር አመራር በሌሎች የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይም ሊደገም እንደሚገባ አሳስበዋል።

በምርጫው ሂደት የተገኙ ልምዶችና ተሞክሮዎች ለቀጣይ የልማት ሥራዎች ጠቃሚ መሠረት መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በዞናችን በሁሉም ዘርፎች የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በተለያዩ ጊዚያቶች በታቀዱ የ100 ቀን እና የ120 ቀናት ዕቅዶች በማቀድ ውጤታማ ሥራዎች ተሰርተው ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በድህረ-ምርጫ ወቅት አስፈጻሚ ተቋማት እና መዋቅሮች የህዝቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት እና በተለይም የግብርና እና ለሎች የክረምት ወቅት ሥራዎችን በአንድ ወራት ውስጥ የሚፈፀሙ ልዩ ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር በመግባት መረባረብ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በ120 ቀናት ዕቅድ ታቅደው የቀሩ ተግባራትን በተመለከተም እያንዳንዱ አመራር ልዩ ዕቅድ በማዘጋጀት ቀሪ ሥራዎችን በከፍተኛ ትኩረትና በተሻለ ቅንጅት ማስፈፀም እንደሚገባ አቅጣጫ ተሰጥቷል።

በተለይም የፋይዳ ምዝገባ፣ የኢትዮ ኮደርስ ፕሮግራም፣ የሌማት ትሩፋት እና ሌሎች የተቀመጡ ኢኒሼቲቮች ውጤታማ እንዲሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረ ክትትልና ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።

በመጨረሻም የዕቅዶቹን ስኬታማ አፈፃፀም ለማረጋገጥ በጋራ ውይይት፣ በተቀናጀ አሠራር እና በተጠናከረ ክትትል መሥራት እንደሚገባ በመግለጽ ውይይቱ ተጠናቋል።

Photos from Demba Gofa Woreda Government Communication Affairs Office's post 04/06/2026

ምክር ቤቱ የብድር ስምምነቶችን አጸደቀ
**************

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ጉባኤው በኢትዮጵያና በአፍሪካ ልማት ባንክ መካከል ለአርብቶ አደሩ የምግብና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ለስድስተኛ ምዕራፍ የልማት ሴፍትኔት ፕሮጀክት የተደረገ የብድር ስምምነትም ምክር ቤቱ አፅድቋል።

የብድር ስምምነቶቹን በማስመልከት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከአፍሪካ ልማት ባንክ ለአርብቶ አደር ምግብና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተገኘው ብድር መንግሥት የአርብቶ አደሩን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ የተቀናጁ የልማት ፕሮጀክቶችን ይበልጥ ለማገዝ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

በተለይም በ30 ወረዳዎች ውስጥ ተግባራዊ እየሆነ የሚገኘው የአርብቶ አደሩን የምግብና የኑሮ ዘይቤ ማሻሻያ ፕሮጀክት አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ዋና ተጠሪው አብራርተዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም ይህንን የልማት ተግባር ይበልጥ ለማጠናከር እና በክፍል አንድ ያልተካተቱትን ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን በማካተት የአርብቶ አደሩን የአደጋ ተጋላጭነትን የመቋቋም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በአፍሪካ ልማት ባንክ 71 ሚሊዮን 940 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

በብድር የተገኘው ገንዘብ የውሃ መሠረተ ልማቶችን፣ የእንስሳት ጤና አገልግሎቶችን፣ ዘላቂ የመሬት አያያዝን፣ አግሪ ቢዝነስ ልማትን፣ ታዳሽ የኃይል አማራጮችን እና የአየር ትንበያ ጣቢያዎችን ለማስፋፋት እንደሚውል ገልፀው፤ ብድሩ ከወለድ ነፃና የአሥር ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡

የብድር ስምምነቱ ከአገራችን የብድር ስትራቴጂ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣምና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቀነስና የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በብድር ስምምነቱ ላይ ከተወያየ በኋላ ረቂቅ አዋጁ፣ አዋጅ ቁጥር 1423/2018 ሆኖ በሙሉ ድምፅ መጽደቁን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል።

በተያያዘም የመንግሥት ዋና ተጠሪ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር መካከል ስድስተኛውን ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክትን ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዚህም መንግሥት በምግብ እጥረት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ከዕርዳታ ተጠቃሚነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር ባለፉት ጊዜያት የልማት ሴፍትኔት ፕሮጀክትን ቀርጾ ተግባራዊ ማድረጉንና ስድስተኛው ምዕራፍ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት በ12 ክልሎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር ውስጥ ባሉ 494 ወረዳዎች ተግባራዊ ይሆናል፡፡

በመጨረሻም በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር የተደረገው የብድር ስምምነት አዋጅ ቁጥር 1424/2018 አድርጎ በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ምክር ቤቱ አጽድቆታል፡፡

04/06/2026

ከድምፅ መስጫ እስከ ውጤት ማፅደቅ ያለው ዑደት

Want your business to be the top-listed Government Service in Addis Ababa?

Click here to claim your Sponsored Listing.

Location

Address


Addis Ababa