06/06/2026
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰጠ የሐዘን መግለጫ
. **************
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በኦሮሚያ ክልል በወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት ክብርት ዳኛ ወርቄ ፈከንሳ በችሎት የዳኝነት ሥራ እየሰሩ ሳሉ በባለጉዳይ በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው በማለፉ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን።
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲህ አይነቱ በዳኞች ወይም በሌሎች የፍትሕ ሥርዓት ተዋናዮች ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ድርጊቶች የሕግ የበላይነትን ለማዳከም የሚደረጉ ተግባራት እንደሆኑ በማመን በጽኑ እናወግዛለን።
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሟች ዳኛ ወርቄ ፈከንሳ ቤተሰቦች፣ የሥራ ባልደረቦች እና ለመላው የፍትሕ ማህበረሰብ መጽናናትን ይመኛል።
05/06/2026
ክብርት ዳኛ ወርቄ ፈከንሳን በተመለከተ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠ መግለጫ
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኦሮሚያ ክልል በወልመራ ወረዳ ፍርድ ቤት ክብርት ዳኛ ወርቄ ፈከንሳ የዳኝነት ሥራቸዋን በሕግና በሙያ ሥነ-ምግባር መሠረት በማከናወን ላይ እያሉ ግንቦት 27 ቀን 2018 ዓ.ም በባለጉዳይ በተፈጸመ የጦር መሣሪያ ጥቃት ሕይወታቸው በማለፉ የተሰማን ሐዘን ጥልቅ ነው::
የዳኞች ደህንነትና ነፃነት የፍትሕ ሥርዓቱ መሠረታዊ ዋስትና ሲሆን፣ ዳኞች ከማንኛውም ዓይነት ዛቻ፣ ጫና ወይም ጥቃት ነፃ ሆነው የሕግ ተግባራቸውን ማከናወን ይገባቸዋል። ሆኖም የተፈጸመው ድርጊት በአንድ ዳኛ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ብቻ ሳይሆን በሕግ የበላይነት፣ በዳኝነት ነፃነት እና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የተቃጣ ከባድ ጥቃት እንደሆነ እንረዳለን።
እንዲህ አይነቱ በዳኞች ወይም በሌሎች የፍትሕ ሥርዓት ተዋናዮች ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ድርጊቶች የሕግ የበላይነትን ለማዳከም የሚደረጉ ተግባራት እንደሆኑ በማመን በጽኑ እናወግዛለን።
ፍርድ ቤቱ ይህንን አሳዛኝ ድርጊት በጽኑ እያወገዘ፤ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት በፍጥነት፣ በተሟላ እና በግልጽ ሁኔታ እንዲጣራ እና ተጠያቂዎችም በሕግ ፊት እንዲቀርቡ ጥሪ ያቀርባል።
በተጨማሪም በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዳኞችና ሌሎች የፍትህ ዘርፍ ባለሙያዎች ደህንነት እንዲጠናከር እና ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይደገሙ አስፈላጊ የጥበቃ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እያሳሰብን፤ ፍርድ ቤቱ ለሟች ዳኛ ወርቄ ፈከንሳ ቤተሰቦች፣ የሥራ ባልደረቦች እና ለመላው የፍትሕ ማህበረሰብ መጽናናትን ይመኛል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት
ግንቦት 28 ቀን 2018 ዓ.ም
01/06/2026
#በዛሬው ዕለት በሚካሄደው 7ተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ድምጽ መስጠት ከተጀመረበት ጀምሮ
#በገረሴ ወረዳ ፍ/ቤት አንድ ተከሳሽ
#በደራማሎ ወረዳ ፍ/ቤት አንድ ተከሳሽ በድምሩ ሁለት ተከሳሾች የምርጫ ቦርድ ስርአቱን በመጣስ ከተከሰሱበት ውጭ ምንም አይነት ጉዳይ በጋሞ ዞን ስር ባሉት ወረዳም ሆነ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች እንዲሁም በይግባኝ በዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበ ክስ አለመኖሩን እንገልጻለን።
ግንቦት 24/2018ዓ.ም (ጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት)
29/05/2026
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዲታ ወረዳ ፍ/ቤት የመስክ ምልከታውን አደረገ::
ግንቦት 05/2018 ዓ.ም(ጋም ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት)
**************,
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት ኘሬዝዳንት ክቡር አቶ ግንሶ ግዛው በዲታ ወረዳ ፍ/ቤት መስክ ምልከታ ያካሄዱ ሲሆን በምልከታቸውም ምቹ የተዘዋዋሪ ማስቻያ ችሎቶች ዘመናዊ የተገልጋዮች ቀጠሮ ማሳያ ዲስኘሌይ የግቢ ውበት ምቹ የተገልጋይ ማረፊያ ተመልክተዋል::
በስተመጨረሻም ከፍ/ቤቱ ኘሬዝዳንት ዳኞች እና በጉባኤ ከሚተዳደሩ ባለሙያወች እንዲሁም ማኔጅመንት አባላት ጋር በተቋሙ በ9ወራት ውስጥ የተሰሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተነስተው ውይይት ተደርጎ ለቀጣይ ስራዎች አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱን አጠናቋል::
29/05/2026
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት ክቡር አቶ ግንሶ ግዛው በቁጫ ወረዳ ፍ/ቤት እና በሠላምበር ከ/አስ/የመ/ደ/ፍ/ቤት የስራ ጉብኝት አደረጉ::
ግንቦት 21/2018 ዓ.ም
. ****************************
የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግንሶ ግዛው በሁለቱም ፍ/ቤቶች በአካል በመገኘት የተቋሙን የሥራ እንቅስቃሴ የመስክ ምልከታ አካሂደዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የፍርድ ቤቱ የበጀት አጠቃቀምና ለታቀዱ ፕሮጀክቶች የዋለበት ሁኔታ የተገመገመ ሲሆን፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን የሥራ ግንኙነት በማጠናከር ረገድም የተከናወኑ ተግባራት ተቃኝተዋል።
በተጨማሪም ለሠራተኞች እና ለባለጉዳዮች ምቹ የሥራ ሁኔታን ከመፍጠር አንጻር ያለውን ደረጃ የመመልከት ሥራ ተከናውኗል።
ፍርድ ቤቱን በቴክኖሎጂ በማዘመን ረገድ ከፍተኛ አጽንኦት የሰጡት ኘሬዝዳንቱ፤ በቀጣይ የፍትህ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ በትኩረት መሥራት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በአጠቃላይ በጉብኝቱ የሁለቱንም ፍርድ ቤቶች የአሰራር ጥንካሬዎችና ድክመቶች በመለየት፣ ቀልጣፋ የፍትህ አገልግሎት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በውይይቱ ላይ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት የሁለቱም ፍ/ቤት ኘሬዝዳንቶች ዳኞች በጉባኤ የሚተዳደሩ ባለሙያወች የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል።
28/05/2026
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በደረማሎ ወረዳ ፍ/ቤት እና በዋጫ ከተማ አስ/የመ/ደ/ፍ/ቤት ድጋፍ ክትትል አደረገ::
ግንቦት 20/2018 ዓ.ም (ጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት)
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግንሶ ግዛው በዋጫ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እና በደረማሎ ወረዳ ፍርድ ቤት በአካል በመገኘት የመስክ ምልከታ፣ የሥራ አፈፃፀም ግምገማ እንዲሁም ድጋፋዊ ክትትል አድርገዋል።
የድጋፍና ክትትሉ ዋና ዓላማ በፍርድ ቤቶች የተከናወኑ የመስክ ምልከታዎችንና የድጋፍ ክትትል ውጤቶችን መነሻ በማድረግ የፍትህ ሥርዓቱን የበለጠ ለማጠናከር የታለመ መሆኑ ተገልጿል።
በቆይታቸውም በሁለቱ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ በተዘዋዋሪ ችሎት አፈፃፀም፣ በፋይል አያያዝ፣ በተገልጋይ አስተናጋጅነት ዙሪያ በተግባር ተመልክተዋል።
ከሁለቱም ፍ/ቤቶች ኘሬዝዳንቶች ዳኞች የማናጅመንት አካላትና በጉባኤ ከሚተዳደሩ አካላት ጋር የጋራ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት ለሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰሩ ያሉ የዳኝነት አገልግሎት ስራዎች፣ የውሳኔ አሰጣጥ ቀልጣፋነት እና ከፍትህ አሰጣጥ ጋር የሚታዩ ችግሮች ላይ ጥልቅ ውይይት ተካሂዷል።
ኘሬዝዳንቱ የፍትህ አገልግሎትን በፍጥነትና በቀላሉ እንዲያገኙ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ስርዓቶችን ማስፋፋት የግድ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
እንዲሁም የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማዘመንና የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ለተደራሽና ፍትሐዊ የፍትህ አገልግሎት ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ አካላትም በፍትህ ስራው የተገኙ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል የሚታዩ ክፍተቶችን ማረም የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።
28/05/2026
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ኘሬዝዳንት ክቡር አቶ ግንሶ ግዛው በቁጫ አልፋ ወረዳ ፍ/ቤት ድጋፍና ክትትል አደረጉ።
ግንቦት 20/2018 ዓ.ም(ጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት)
የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግንሶ ግዛው በቁጫ አልፋ ወረዳ ፍ/ቤት በመገኘት የዳኝነት የሥራ አፈጻጸም ግምገማና ድጋፋዊ ክትትል አድርገዋል።
በክትትልና ድጋፉ የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግንሶ ግዛው የድጋፍና ክትትል ዋና ዓላማ በፍ/ቤቱ የተከናወኑ አፈጻጸሞችን መነሻ በማድረግ የዳኝነት አሰጣጥንና የፍትሕ ሥርዓቱን የበለጠ ለማጠናከር የታለመ መሆኑን ገልጸዋል።
በፍርድ ቤቱ የዳኝነት አሰጣጥ ቅልጥፍና፣በስታንዳርድ ከመወሰን አኳያ፣የተዘዋዋሪ ችሎት አገልግሎት አፈጻጸም፣የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ መዝገብ፣ ፋይል አያያዝ፣ባለጉዳዮችን በሥነ ምግባር በአግባቡ ከማስተናገድ አኳያ ያሉ ችግሮች ፣ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ከመፈጸም አንጻር ያሉ አፈጻጸሞች ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ አንስተው በጥልቀት ገምግመዋል።
አያይዘው ህብረተሰቡ ከልማት ሥራው ጎን ለጎን በተዘዋዋሪ ችሎቶች የፍትሕ አገልግሎት እንዲያገኝ የተዘዋዋሪ ችሎት በተጠናከረ መልኩ ሳይንጠባጠበ መቀጠል እንዳለበት ፣ፍርድ ቤቶች የሕዝብንና የመንግሥትን ጥቅም በሚነኩ ጉዳዮች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ማለትም ከፍትሕ እና ከፖሊስ ጽ/ቤት ጋር በሦስትዮሽ ውይይት ተቀናጅተው መስራትና በዳኝነት ሥራው የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ እንዳለባቸው በአጽንኦት ገልጸዋል።
በድጋፍና ክትትሉ ላይ የጋሞ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ግንሶ ግዛው ፣የቁጫ አልፋ ወረዳ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ አምሳሉ አንጅሎ የፍርድ ቤቱ ዳኞች፣ረዳት ዳኞች እና የማኔጅመንት አካላት በመድረኩ ላይ ተሳትፈዋል።